ከምንጊዜውም በላይ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም መጠበቅ አለብን - ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ

104

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):- ከምንጊዜውም በላይ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም መጠበቅ አለብን ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸይኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናገሩ። 

በኢትዮጵያ አራተኛው ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም "ኢፍጣራችን ለአንድነታችን" በሚል መሪ ሃሳብ  በአዲስ አበባ ተካሂዷል።


 

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ የመሰባሰቢያና የአብሮነት ማሳያ በሆነው የረመዳን ወር በጋራ በማፍጠራችን ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ብለዋል።

በታላቁ ወር እያደረግን ባለው ፆም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝና በመደገፍ ሊሆን ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የተቸገሩ ወገኖችን ከማገዝ ባለፈ ከምንጊዜውም በላይ ትብብርና አንድነታችንን በማጠናከር የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም በመጠበቅ ሊሆን ይገባል ብለዋል። 

ለኢፍጣር ፕሮግራሙ መሳካት የተባበሩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የጸጥታ አካላትን አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ  እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን፤ የኢፍጣር መርኃ ግብር የአንድነታችን እና አብሮነታችን ማጠናከሪያ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም በታላቁ የረመዳን ወር ፆማችን ተቀባይነት እንዲያገኝ ዱአ ከማድረግ ባለፈ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት የድርሻችንን እናበርክት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ አማካሪና የታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርኃ-ግብር የበላይ አስተባባሪ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ፤ የረመዳን ፆም የመሰባሰቢያና የአብሮነት ወር ስለመሆኑ አንስተዋል።


 

የረመዳን ወር አንድነት የሚንጸባረቅበት፣ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም ከማፍጠር በተጨማሪ በቁርዐን ውድድር ላሸነፉ እውቅና እና  ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም