በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል- ቢሮው

89

ዲላ፣መጋቢት 19/2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበልግ እርሻ እስካሁን ድረስ ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በክልሉ በመስኖ ለምቶ ለገበያ እየቀረበ ያለው ምርት ዋጋ እያረጋጋ መሆኑም ተመላክቷል።

የቢሮው ሃላፊ  አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ከ741 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ እርሻ ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

የእርሻ ዝግጅቱ 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ከ350 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳም በዋና ዋና ሰብሎች በዘር ለመሸፈን መቻሉን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የሚያስፈልገው ከ401 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎች እንዲሁም ምርጥ ዘር እየቀረበ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከልማቱም ከ68 ሚሊዬን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ያመለከቱት አቶ ሃይለማርያም ይህም ከአምናው የበልግ እርሻ የ15 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ አርሶ አደሩ ግብዓትና ቴክኖሎጂን በአግባቡ እንዲጠቀም በግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው። 

በበልግ ለማግኘት የተያዘውን ምርት ለማሳካት ባለድርሻ አካላትና አመራሩ ሳይለማ የሚቀር መሬት እንዳይኖር ተገቢ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ በተያዘው ዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ አምራች ለመሆን ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም ከ127 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማቱን አስታውሰው፣ በመስኖ ለምተው ለገበያ የቀረቡት የድንች፣ የቲማቲም እና የበቆሎ ምርቶች ገበያውን እያረጋጉ ናቸው ብለዋል።


 

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመስኖ የለማ ሰብልን ከማሳ አንስቶ የበልግ እርሻን ለማጠናከር በንቅናቄ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። 

በዞኑ በበልግ ወቅት 12 ሺህ 223 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ርብርብ እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ በደቻ ናቸው።

አርሶ አደሩ መሬቱን ደጋግሞ የማረስ ተሞክሮው እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ ለልማቱም አስፈላጊው ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው ብለዋል።

በተለይ በአርሶ አደሩ እጅ የሚገኘውን የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በቅብብሎሽ ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ በግዥ ጭምር ለአርሶ አደሮች እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ የወናጎ ወረዳ አርሶ አደር ሃይሉ ዋቆ በበኩላቸው በበልግ እርሻ አራት ሄክታር ማሳቸውን በብርዕ፤ በአገዳ እና በሥራ ስር ሰብሎች ለመሸፈን በደቦ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በበልግ እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ማሳቸውን ደጋግመው ከማረስ ባለፈ በኩታ ገጠም ለማልማት የዝግጅት ሥራ ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩ እጅ ያሉ የግብርና ግብዓቶችን እርስ በርስ በመዋዋስ በአሁኑ ወቅት ወደ ዘር ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፣ ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያና የተለያዩ ምርጥ ዘሮች እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም