የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ በይፋ ተመሰረተ

116

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-የሴቶችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ (ኒውፊን) በይፋ ተመሰረተ።

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ባለሙያ ሴቶች ኔትዎርክ (ኒውፊን) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በዓለም ባንክ ትብብር የተመሰረተ ሲሆን የፋይናንስ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ሴቶች የራሳቸው ድርሻ እንዲያበረክቱ ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑም ተነስቷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በፋይናንስ አካታችነት መርሐግብር በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው የተሳትፎና የተጠቃሚነት ድርሻ ተመጣጣኝ አለመሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂው መሰረት በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ልዩነት የማጥበብ አላማን የሰነቀ መሆኑን ተናግረዋል። 

ዘላቂነትና መተማመን ያለበት የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት በባንኩ አካታች የፋይናንስ ስርዓት ለመገንባት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን ወደ አመራርነት በማምጣትም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሴቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻል መሆኑን አንስተዋል።

የሴቶች የፋይናንስ አካታችነትን ከግብ ለማድረስ የኔትዎርኩ መመሥረት ትልቅ አስቻይ አደረጃጀት እንደሆነ አብራርተዋል።

የኔትወርኩ ዓላማ ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ የሚያበቃና የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍን የፋይናንስ ዘርፍ ማጎልበት እንደሆነ ገልፀው፣ ለዚህ ጥረት የዓለም ባንክን ድጋፍ አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም