ቀጣናዊ ሰላምና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር የሚኖረው ፋይዳ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

226

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-  ቀጣናዊ ሰላምና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር የሚኖረው ፋይዳ ላይ ያተኮረ  የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከሰላም ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ "ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር" በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።


 

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሐ ይታገሱ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በፓናሉ ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር በሚኖራቸው አስተዋጽኦ ላይ ያተኮሩ የውይይት መነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል። 


 

የውይይት መነሻ ጽሁፎቹም ቀጣናዊ ሰላምና የህዝቦች አብሮነት እንዲሁም ቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነት በሚሉ ርዕሶች እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።

በዚህም የምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ቅኝት ከሰላም አንጻር ምን መልክ እንዳለውና ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ በውይይቱ የሚዳሰስ ይሆናል። 

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ኢትዮጵያ ያላት ጽኑ አቋምና ይህም ለአህጉራዊና ቀጣናዊ ሰላም የሚኖረው አስተዋጽኦ የውይይቱ ማጠንጠኛ እንደሚሆን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሀገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያላቸው መድረኮችን ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም