የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በዛሬው እለት መካሄድ ይጀምራል

188

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 19/2016(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በኋላ በ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ወደ ውድድር ይመለሳል። 

በመርሃ ግብሩ መሰረትም መቻል ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚሰለጥነው መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው በሶስቱ ተሸንፏል።

ክለቡ በ36 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በያሬድ ገመቹ የሚሰለጥነው ወላይታ ድቻ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ጨዋታ አላሸነፈም። በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።

ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሌላኛው የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

በአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት ገጥሞታል። አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ቡናማዎቹ በ29 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በውበቱ አባቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ክለቡ በ30 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታ ነገም ቀጥሎ ሲውል አዳማ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት፤ ሀዲያ ሆሳዕና ከሀምበሪቾ ዱራሜ  ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ 19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ37 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

የሀዋሳ ከተማው አሊ ሱሌይማን በ10 ግቦች የፕሪሚየር ሊጉን ከፍተኛ የግብ አስቆጣሪነት እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም