በክልሉ ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠና ተሰጥቷቸው ለውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ተዘጋጅተዋል---ቢሮው

149

ሆሳዕና፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግማሽ በጀት ዓመቱ ከ27 ሺህ በላይ ዜጎች ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ስልጠና ተሰጥቷቸው ለሥራ መዘጋጀታቸውን የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው በአጫጭር ስልጠናዎች አሰጣጥና ምቹ ሁኔታ መፍጠርን በማስመልከት በክልሉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ መክሯል።


 

የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎምባ ደምሴ እንደገለጹት፣ ቢሮው ለውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት የሥራ ገበያውን መሰረት በማድረግ የሰለጠኑና በከፊል የሰለጠኑ ዜጎች የሚስተናገዱበትን አሠራር እየዘረጋ ይገኛል።

በእዚህም በውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ፍላጎትን መሰረት ክህሎት መር አጫጭር ስልጠናዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

በተያዘው ዓመት ብቻ የውጪ ሀገራት የሥራ ስምሪትን ማዕከል ያደረገ አጫጭር ስልጠና ለ42 ሺህ ዜጎች መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ስልጠና ከወሰዱት መካከል 27 ሺህ 500 የሚሆኑት ዜጎች ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን አሟልተው ለውጪ ሀገራት የሥራ ስምሪት ዝግጁ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ስልጠናው የዜጎችን ደህንነት፣ ክብርና ውጭ አገር ከሄዱ በኋላ መብታቸው ተከብሮና በተሻለ ገንዘብ ተቀጥረው ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር ነው።

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ለሚገኙ የሥራ ስምሪት አማራጮች እውቀትና ክህሎት ያለው ባለሙያ ለማሰማራት ክልሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

"ይህም የዜጎችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ህገ ወጥ ስደትን ለመከላከልና የሥራ አጥነት ችግርን ደረጃ በደረጃ ለማቃለል ያስችላል" ብለዋል።

ስልጠና ሳይወስዱና ክህሎት ሳይኖራቸው ወደ ሥራ የሚሰማሩ ወጣቶች በአቅም ማነስ ምክንያት ተጠቃሚ እንዳልሆኑም ተናግረዋል። 

የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶፊቅ ጁሀር በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክህሎት ላይ የተመሰረተ የሥራ ስምሪት መመቻቸቱ ከሙያ ብቃት ጋር ተያይዞ ያሉትን ክፍተቶች ለመሙላት ያግዛል።

በመሆኑም በክልሉ በሚገኙ 38 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከመደበኛ ስልጠና በተጨማሪ ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ አጫጭር ስልጠናዎች እየተሰጡ ናቸው ብለዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ ከክልሉና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም