አንድነቷና ሰላሟ ተጠብቆ የበለጸገች አገርን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

330

ባህርዳር ፤ መጋቢት 18/2016 (ኢዜአ)፡- አንድነቷና ሰላሟ ተጠብቆ የበለጸገች አገርን ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የ403ኛ ኮር ዋና አዛዥ እና የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሃላፊ ጄኔራል አዝዘው መኮንን ገለጹ።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ከደብረ ማርቆስ ከተማ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ማስከበርና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በምዕራብ እዝ የ403ኛ ኮር ዋና አዛዥ እና የምስራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አዝዘው መኮንን በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ከነ ሙሉ ክብሯ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

አሁን ላይ በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ ችግር የኢትዮጵያን እድገት እና ልማት ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ጸረ-ሰላም ሃይሎች የተጠነሰሰ ሴራ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ሙሉ በሙሉ በማቃለል የበለጸገች አገር ለመገንባት በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት አሁን ላለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንድንበቃ አስችሏል ብለዋል። 

ህብረተሰቡም ጸረ ሰላም ሃይል በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ  መንበሩ ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በከተማዋ ባለፉት ሰባት ወራት ተፈጥሮ በቆየው የጸጥታ ችግር ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ደርሷል። 

ይሄን ችግር ለማቃለል በሚደረገው ጥረትም የንግዱ ማህበረሰብ የአጥፊ ሃይሎችን ፕሮፓጋንዳ በመተው ለሰላም ትልቅ ዋጋ ያለውን ግብር በወቅቱ መክፈል እንዳለበት ጠቁመዋል።

ግብር ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት፣ ልማትን ለማፋጠንና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ለማስፈን ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ሰላምን ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የበኩላችን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም