በአማራ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ በማድረስ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነው - አቶ አረጋ ከበደ

170

ባህርዳር፤ መጋቢት 18 /2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ሰብአዊ እርዳታ በማድረስ ችግሩን ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የሚደረገውን ጥረት የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ማገዝ እንደሚጠበቅባቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኮሚሽን የስራ ሃላፊዎች ጋር ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ያደረጉትን ውይይት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ክልሉ በሰሜኑ ጦርነትና ቀጥሎም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል።


 

ክልሉ አጋጥሞት ስለነበረው ችግር በውይይታቸው ወቅት በዝርዝር ማንሳታቸውን ገልጸው፤ ጉዳቱን ለመቀነስ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ተግዳሮትን ጨምሮ በክልሉ ሲያጋጥም የቆየውን ችግር በቂ ግንዛቤ ባለመያዙ ምክንያት በአለም አቀፍ ድርጅቶች ተገቢውን ድጋፍ ያለመደረጉን በማንሳትም መግባባት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።

የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎችም ችግሩን በመረዳት በቀጣይ በክልሉ ለሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍና ችግሮችን ለመቀነስ በሚከናወነው ስራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ሚስተር ማርሴል አክፖቮ በበኩላቸው ፤ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገራት ኢትዮጵያ ታላቅና ወሳኝ አገር መሆኗን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰላም መሆን በሌሎች የቀጣናው አገራት ላይ ሰላምና ማረጋጋት እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ ለኢትዮጵያ ሰላም መጠበቅ ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደረግ ተናግረዋል።

በአማራ ክልልም ቀደም ሲል በነበረው ችግር ምክንያት ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን መገንዘብ እንደቻሉ ገልጸው፤ ችግሩ እንዲፈታ ድርጅታቸው እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም