ቀጥታ፡

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኃብት ማሰባሰቢያ የቦንድ ሣምንት ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንድ መቶ ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተዘጋጀ የቦንድ ሣምንት ዛሬ ተጀመረ።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 13ኛ ዓመት በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም፤ በቦንድ ሣምንቱ መቶ ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።

የቦንድ ሣምንቱ ከዛሬ መጋቢት 18 ጀምሮ በመላ አገሪቱ እንደሚካሄድ ጠቅሰው የቦንድ ሽያጩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና ንግድ ባንክ እንዲሁም በሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ኃብት ማሰባሰቢያ የሚውል በቂ የቦንድ ኩፖን ተዘጋጅተዋል ብለዋል።


 

ኅብረተሰቡ በሁሉም የልማት ባንኮች ቦንዱን ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ሒሳብ አስተዳደር ሥርዓት ዳይሬክተር ቤተል ታደሰ ኅብረተሰቡ በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎቹ ቦንድ መግዛት እንደሚችሉ ገልጸዋል።


 

በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በተዘጋጀላቸው የኦንላይን ሥርዓት በሚፈልጉት ምንዛሪ ቦንዱን መግዛትና ለግድቡ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ነው ያስረዱት።

ባለፉት ስምንት ወራት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ 931 ሚሊየን ብር በላይ ከኅብረተሰቡ ማሰባሰብ መቻሉን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባለፉት 13 ዓመታት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም