ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሂደቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር መስራቱን ይቀጥላል - ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

249

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ  የመማር ማስተማር ሂደቱን በዲጂታል ለማስተሳሰር የተጀመረውን እንቅስቃሴ  እውን ለማድረግ  ከቴክኖሎጂ  ተቋማት ጋር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩንቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት  ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ።

ሁዋዌ ኢትዮጵያ ''በኢትዮጵያ የዲጂታል ትምህርት ትግበራን ማፋጠን '' በሚል መሪ ሃሳብ የዲጂታል ሳምንት ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

በመርኃ ግብሩ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና የባህል ተቋም ተወካይ፣ የዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና በቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢኖቬሽን መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የዩንቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ እኤአ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የመማር ማስተማር ሂደቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በዚህም ዩንቨርሲቲው ከሁዋዌ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር በመተባበር ስማርት የመማሪያ ክፍሎችንና የዳታ ማዕከላት ዝርጋታን ተግባራዊ ለማድረግ የጀመራቸው ሂደቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ዩንቨርሲቲው ለዲጂታል የትምህርት ሴክተር ትኩረት በመስጠት እንደ ሁዋዌ ካሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋራ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስ  የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ተወካይ ዶክተር ሪታ ቢሶናት በበኩላቸው፣ በአሁኑ ጊዜ ትምህርትን በዲጂታል መደገፍ የዓለም አገራት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአፍሪካ የትምህርት ምህዳሩን ለማስፋትና ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለመስጠት በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም እንደ ሁዋዌ ያሉ ኩባንያዎች በአፍሪካ የዲጂታል ትምህርት ግንባታን ለማሳለጥ ያላቸው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዩኔስኮ ከሁዋዌ ኩባንያ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ የአይሲቲ መሰረተ ልማት ግንባታንና ሌሎች ፕሮጀክቶችን እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ የሁዋዌ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ማይክል ሊዩ ኢትዮጵያ በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወጥና እየሰራች መሆኗ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

በዚህም ሁዋዌ በኢትዮጵያ የአይሲቲ መሰረተ ልማትና የዳታና የክላውድ ቤዝ መሰረተ ልማቶችን ዝርጋታ እና በዩንቨርሲቲዎች የስማርት ክፍሎችን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያ በኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ግንባታ መሳተፍ ከጀመረ 25 አመታት አስቆጥሯል።

በአሁኑ ወቅት ከ30 ዩንቨርሲቲዎች ጋር በመጣመር የዲጂታል ትምህርት ዝርጋታን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም