ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የታችኛው ተፋሰስ አገራት በቅርበት ሊደግፉና ወጪ ሊጋሩ ይገባል

225

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የምታከናውናቸውን የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የታችኛው ተፋሰስ አገራት በቅርበት ሊደግፉና ወጪ ሊጋሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

የተፋሰስ ስነ-ሕይወታዊና አካላዊ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሌሎችም ግድቦች የላቀ ጥቅም ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በአካባቢ ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥና ምግብ ዋስትና ዙሪያ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን ያሳተሙት ዶክተር መንግስቱ ውቤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ወንዞች ለጎረቤት አገራት የልማትና የውሃ ምንጭ ናቸው።

በዚህም በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የአካባቢ ጥበቃ እና የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች ለድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዘላቂ ፍሰት ዋስትና መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአብነትም በላይኛው አባይ ተፋሰስ የሚሰሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ሕዳሴ ግድብን ብቻ ሳይሆን ለሱዳንና ግብፅ ግድቦችም የሚበጅ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችው የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ ከራሷ አልፎ የቀጣናውን አገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የአካባቢው አገራት የኢትዮጵያን የልማት ጥረቶች ማገዝና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

በአገራቱ በኩል እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አለመደረጉን ያስታወሱት ተመራማሪው፤ በቀጣይ ግን አብረው ለመሥራትና ለመደገፍ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በአረንጓዴ ልማት የዲፕሎማሲ ጥረት ኢትዮጵያ በቀጣይ ብዙ መሥራት እንዳለባት ጠቅሰው፤ የታችኛው ተፋሰስ አገራትም በቅርበት ሊደግፉና ወጪ ሊጋሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በዓለም ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየበረታ መምጣቱን የሚናገሩት ዶክተር መንግስቱ፤ የመከላከል ሥራውም ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በአህጉራዊ የአረንጓዴ ልማት ሥራ ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት የመሪነት ሚና እየተወጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ድጋፍና ትብብር ሊደረግላት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተገነቡ ግድቦች እና የተፈጥሯዊ ሐይቆች በደለል እንዳይሞሉ የሚደረገው ጥረት ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገራት የላቀ ጥቅም ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ፈተና ሆኖ የቀጠለ ቢሆንም በተለይም በሰሜን እና የምስራቅ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ድርቅና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም