ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የስጋ ምርት ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የስጋ ምርት ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው
አዳማ ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የስጋ ምርት ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለፀ።
የስጋ ምርት ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ እየተዘጋጀ ያለውን ረቂቅ አዋጅና የማስፈፀሚያ ደንቦች በግብዓት ለማዳበር ያለመ የዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስጋ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በስፋት ጥቅም ላይ ከመዋሉም ባለፈ ወደ ዓለም ገበያ ተልኮ ለሀገሪቷ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው።
''ኢትዮጵያ የስጋ ምርቶችን በዋናነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ እየላከች ትገኛለች'' ያሉት ዶክተር ፍቅሩ የተቀባይ ሀገራትን የጥራት ደረጃ ያሟላ የስጋ ምርት ለመላክም ሆነ የምርቱን የውጭ ገበያ ተደራሽነት ለማስፋት የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።
በተለይ ተቀባይ ሀገራት በምርቱ ላይ ያላቸውን መተማመን ለማሳደግ ጤንነቱ፣ ደህንነቱና ጥራቱ የተረጋገጠ የስጋ ምርት ተደራሽ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ያስቀመጠውን የጥራት ደረጃ ያሟላ የስጋ ምርት ለመላክ የህግ ማዕቀፎችና አሰራሮች ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሃሚድ ጀማል በበኩላቸው የህግ ማዕቀፉ የስጋ ምርት የወጪ ንግድ ላይ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ብቁና የሰለጠነ የሰው ሃይል በዘርፉ እንዲኖር፣ የቁጥጥር ስርዓቱ የሚመራበት ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ሀገሪቷ እንዲኖራት ለማስቻል የህግ ማዕቀፍ ማሻሻል ማስፈለጉን ገልጸዋል።
በባለስልጣኑ የእንስሳት ምርት ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አያሌው ሹመት ''የነበረው የስጋ ምርት ደህንነትና ጥራት ምርመራ አዋጅና ደንብ ለረጅም ዓመታት ስራ ላይ መቆየቱን ገልጸዋል።
ነባር ህጎች ከዓለም አቀፍ የእንስሳት ጤና ድርጅት መስፈርት አኳያ ማሰራት የማይችሉና በዓለም ገበያ በስፋት ዘልቀው ለመግባት ማነቆ መሆናቸውን አንስተዋል።
አዋጆቹ በ1962 ዓ.ም እንዲሁም ደንቡ በ1963 ዓ.ም የወጣ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አያሌው በ1976 ዓ.ም ውስን ማሻሻያ ተደርጎበት እስከ አሁን በስራ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የህግ ማዕቀፎቹ ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት ልማትና እድገት ጋር የማይጣጣሙ ከመሆናቸውም ባለፈ የተቀባይ ሀገራት አስቻይ ጥያቄዎችን መመለስ የማይችሉ በመሆኑ ማሻሻል ማስፈለጉን ተናግረዋል።