የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ሥላሴ ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

264

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ሥላሴ ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዙ ቢንግን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የሁለቱም ወገኖች ውይይት በተለያዩ በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና አለምአቀፍ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቅሷል።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደር ታዬ የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በወቅቶች እና በሁኔታዎች የማይቀያየር ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ግንኙነት አጠናክሮ ለመጓዝ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዙ ቢንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የቻይና ሁለንተናዊ ትብብር በአፍሪካ እና ቻይና መካከል ላለው ግንኙነት ትልቁ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቻይና የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ኮንፈረንስ እና የቻይና አፍሪካ ትብብር ፎረም ጉባኤዎች በመጪው ሰኔ እና መስከረም በቤጂንግ እንደሚካሄዱ በውይይቱ ተጠቁሟል።

ለጉባኤዎቹ ስኬት ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና እንዳላት የጠቀሱት ልዩ መልዕክተኛው ለዚህም የድርሻዋን እንድታበረክት መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም