ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ህዝቡ የመንግስትን የልማት አቅጣጫ እንዲረዳ የሚያደርጉ መሆናቸው ተገለጸ

177

ነቀምቴ፣መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሚያደርጓቸው ውይይቶች ህዝቡ የመንግስትን የልማት አቅጣጫ እንዲረዳ የሚያደርግ መሆኑን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ገለጹ።

እየተደረጉ ያሉ ውይይቶች ህዝብና መንግስት የበለጠ እንዲቀራረቡ እድል የሚፈጥሩ መሆኑም ተገልጿል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፈቀደ ሁንዴ እንዳሉት "ሁል ጊዜም መወያየት የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነው"።

በየትኛውም ዓለም ቢሆን መንግሥት ህብረተሰቡን በአንድነት በልማት ላይ ለማሳለፍና የሚፈለገውን ሀገራዊ የጋራ ተልዕኮ ከስኬት ለማድረስ ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ባለፉት ሳምንታት ያደረጓቸው ውይይቶች ሀገሪቷ እያደረገች ያለውን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን ለማስጨበጥና እያጋጠሙ ያሉትን ፈተናዎች ለመፍታት የሚያግዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በየአካባቢው የሚከሰቱት የሰላምና ፀጥታ ችግሮች እልባት እንዲያገኙ ውይይቶቹ ትልቅ ጠቀሜታ አላቸው ሲሉም አክለዋል።

በተጨማሪም እንደ ሀገር የተጀመሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግቦች እንዲሳኩም መንግስት የህዝቡን ፍላጎት ተረድቶ መፍትሄ የሚሰጥበት መሆኑን አስረድተዋል።

ውይይቶቹ መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ እንዲያተኩሩ የሚረዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም መንግስት የጀመረውን ውይይት ቢያጠናክር መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው በዩኒቨርስቲው የልማትና አስተዳደር መምህር ዶክተር ኦላና ደበላ በበኩላቸው ውይይቶቹ እኩል ተሳታፊነትን የሚያጎለብቱ በመሆኑ ለመንግሥት ቀጣይ እንቅስቃሴዎች ግብዓት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን ያስገኛሉ ብለዋል።

''ሀገራችን የጀመረችውን የእድገት ጉዞ አስፍታ እንድትቀጥል እና በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ የልማት ግቦችን ማሳካት እንድትችል የሚያግዝ ነው'' ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ከየአካባቢው ከሚወከሉ የህዝብ ተወካዮች ጋር የሚደረግ ውይይት በሀገሪቷ በሁሉም አቅጣጫ የሚነሱትን የህዝብ ጥያቄዎች በመንግስት በኩል እውቅና እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው ያሉት።

በመንግሥት አስተዳደር ለውጦች ምክንያት የሚፈጠሩ የሀሳብ እና የፖለቲካ የአቋም ለውጦችን አስረድቶ አብሮ በመጓዝ ሂደት ውስጥም ውይይቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።

ሰሞኑን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የባህር በር አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም