በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ለረዥም ጊዜ ፋይዳ ትልም ይዞ የተነሳና ሥራው ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዛሬ ጠዋት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ሥራ ሂደት መገምገማቸውንም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ቀዳሚ አላማችን አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ኑሮ የተመቸች ሳቢ ከተማ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳካት ነው ብለዋል።

የማልማት ሥራ ሂደቱ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በመንግሥት ብሎም አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እና የተለያዩ አካላት የተያዙና የተከራዩ ንብረቶችን የነካ ሊሆን ቢችልም ይህ ለረዥም ጊዜ ፋይዳ ትልም ይዞ የተነሳ ሥራ ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል ብሎም ለሰፊው ሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተጨማሪም እየተስተዋለ ያለው አዲስ የሥራ ባህል ማቆጥቆጥ በመላው ሀገራችን ሊቀዳ እና ሊባዛ የሚገባው መሆኑንም አመላክተዋል።

ቀደም ብሎ እንደተገለፀው በከተማዋ ዐበይት የጉዞ መስመሮችን ለማሻሻል እና የከተማ ውስጥ ዝውውርን ለማሳለጥ ከፍ ያለ ግብ ያስቀመጠ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።

የሥራው መጠነ ርዕይ ኢመደበኛ በሆነ አሰፋፈር ተጎሳቁሎ የሚገኘውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ እያደገና ከተማዋን እያጨናነቀ ለመጣው የትራፊክ ውጥረት መፍትሔ መንገዶችን ማስፋት፣ ለእግረኞች ሰፊ መንገዶችን ማበጀት፣ የቅርስ ቦታዎችን መጠገን ብሎም ህንፃዎችን በከተማዋ የህንፃ ሥነውበት ደረጃ ልክ ማድረስ የሚሉ ተግባራትን ያቀፈ መሆኑ ተመላክቷል።

ከሥራው አስቀድሞም የከተማዋ አስተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ያካሄደ ሲሆን በልማት ሥራው የተነሱ ነዋሪዎችን ለመርዳት የተለያዩ ተግባራትን ማከናውኑም ተገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ የኮሪደሮች ልማት ሥራው የዝናቡ ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ በሚቀጥሉት ወራት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም