ቀጥታ፡

የኔዘርላንድስ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሰራ ነው - አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፡-የኔዘርላንድስ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር  ሄንክ ጃን ባከር ገለፁ።

አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት  ኔዘርላንድስና ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መልካም ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።

ኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ቀዳሚ የልማት አጋር መሆኗን ተናግረው፤ አሁን በምግብ ዋስትና፣ በውኃና በጤና ላይ ትኩረት በመሰጠት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የኔዘርላንድስ የንግድ ማኅበረሰብ መኖራቸውን ገልጸው ወደ 100 የሚጠጉ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እየተሳፉ ነው ብለዋል። 

አብዛኞቹም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በአበባ ልማት ዘርፍ እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ኔዘርላንድስ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ዋነኛ መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸው ሁለቱ ሀገራት በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት። 

በተመሳሳይ የኔዘርላንድስ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳትፏቸውን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።   

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም