ቀጥታ፡

በባሌ ዞን ስራ የጀመሩ አስር ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች የመድኃኒት አቅርቦትን እያሻሻሉ ነው-የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት

ሮቤ፣ መጋቢት 18/2016 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን ስራ የጀመሩ አስር ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች የመድኃኒት አቅርቦትን እያሻሻሉ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ስራ ከጀመሩት አስር መድኃኒት ቤቶች ውስጥ ስምንት በዚህ ዓመት ስራ የጀመሩ ሲሆን ሁለቱ ባለፈው ዓመት ወደ ስራ የገቡ ናቸው ተብሏል።

የዞኑ ጤና ጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በጤና ተቋማት የሚታየውን የመድኃኒት እጥረት ለማቃለል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። 


 

በተለይ በጤና ተቋማት የሚስተዋለው የመድኃኒት ችግር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ጫና ሲያሳድር መቆየቱን አመልክተዋል። 

በዞኑ አስር ወረዳዎች የተገነቡ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶች የህብረተሰቡን ችግር በማቃለል ረገድ ጉልህ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል። 

በተለይ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ዘንድ በተደጋጋሚ የሚነሳውን ቅሬታ መልስ እንዲያገኝ አስችለዋል ብለዋል። 


 

አቶ ደሳለኝ እንዳሉት፣ መድኃኒት ቤቶቹ በቅድመ ክፍያ እንዲሰሩ በመደረጉ የህዝብ ቅሬታዎችን ከመቀነስ ባለፈ ጤና ተቋማቱ ዘላቂና ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እድል ፈጥረዋል ነው ያሉት። 

መድኃኒት ቤቶቹ በዘላቂነት ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ በራሳቸው ከሚያመነጩት ገቢ በተጓዳኝ ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ እያንዳንዳቸው እስከ 300 ሺህ ብር የመነሻ ድጎማ ማግኘታቸውን አቶ ደሳለኝ ጨምረው ተናግረዋል። 

ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት መቋቋሙ ጥራትና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጠ መድኃኒት ለህብረተሰቡ ለማድረስ እድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ በዲንሾ ወረዳ የዲንሾ ጤና ጣቢያ ሞዴል መድኃኒት ቤት ባለሙያ አቶ ነስረዲን ኡመር ናቸው። 

የመድኃኒት ቤቶቹ አገልግሎት መጀመር የወረዳው ጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን በማሻሻል ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

አቶ ታደሰ ደሜ የተባሉ የወረዳው ነዋሪ በሰጡት አስተያየት፣ የጤና መድህን ተጠቃሚ ቢሆኑም የሚታዘዝላቸውን መድኃኒት በጤና ተቋማት ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር ጠቅሰዋል። 

በአካባቢያቸው አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት ከአካባቢያችን ሳንርቅ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እንድናገኝ እያገዘን ነው ብለዋል። 

ሞዴል የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቱ የሚታዘዙልንን መድኃኒቶች በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አስችሎናል ያሉት ደግሞ ሌላው ተገልጋይ አቶ ሁሴን አማን ናቸው። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም