የአንበሳ እና ሸገር አውቶቡሶች የመገልገያ ትኬት ከነገ ጀምሮ ሊቀየር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንበሳ እና ሸገር አውቶቡሶች የመገልገያ ትኬት ከነገ ጀምሮ ሊቀየር ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፡- የአንበሳ እና ሸገር ከተማ አውቶቡሶች የመገልገያ ትኬት ከነገ ጀምሮ የሚቀየር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የአንበሳ እና ሸገር አውቶቡሶች የትራንስፖርት መገልገያ ትኬት ከነገ ጀምሮ ይቀየራል።
የህብረተሰቡን የትራንስፖርት አገልግሎት በማሳለጥ አሰራሩን ለማቀላጠፍና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቋል።
ለዚህም ትኬቶችን መቀየር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ የመዲናዋ የትራንስፖርት ቢሮ በኪሎ ሜትር ባወጣው የትራንስፖርት ታሪፍ መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል።
በመሆኑም አውቶቡሶቹ ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው ትኬት በባለ 5፣ 10፣ 15፣ 20 እና ባለ 25 ብር ይቀይራል ብሏል፡፡
በዚህም መሰረት የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም ድርጅቶች የተቀየረው አዲስ ቲኬት ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡
በአዲስ መልክ ስራ ላይ የሚውለው ትኬት ከነባሩ የተለየ ቀለም፣ ወጥ የሆነ ዋጋ፣ ምስጢራዊ መለያ ያለው መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል።
የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ ዘመናዊ አሰራሮችን ገቢራዊ እያደረገ ሲሆን በቅርቡም /Handheld ticket terminal የተሰኘ ትኬት በቀጥታ አትሞ የሚሸጥ የክፍያ መሰብሰቢያ ቴክኖሎጂም ሥራ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡
የአንበሳ የከተማ አውቶቡስና የሸገር ብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቶች በአዋጅ ቁጥር 74/2015 መሰረት እንዲዋሀዱ መደረጉ ይታወቃል፡፡