በኢትዮጵያ ባለፉት ሶሰት አመታት 296 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሥራ ክንውንና የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት አላቀረቡም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶሰት አመታት 296 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሥራ ክንውንና የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት አላቀረቡም
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦ ከ2013 እስከ 2015 በጀት ዓመት 296 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሥራ ክንውንና የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርት አለማቅረባቸውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
ለመጨረሻ ጊዜ የቀረበውን ጥሪ የማይቀበሉ ድርጅቶችን ባለሥልጣኑ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑ ተገልጿል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩ በተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መሰረት ዳግም ያልተመዘገቡ ድርጅቶች ዳግም እንዲመዘገቡ ለማድረግ ያለመ ነው።
ሪፖርት ማቅረብ ሲገባቸው ያላቀረቡና ህልውናቸውን ያላረጋገጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክንያታቸውን አቅርበው መኖራቸውን እንዲያረግጡ ማድረግ ሌላው የውይይቱ አላማ መሆኑም ተገልጿል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ደኤታ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ነመራ ገበየሁ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገር ልማትና ማህበረሰብን ተጠቃሚ በማድረግ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም በሚጠበቀው ልክ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም ሕጋዊ መንገድን ተከትለው ዳግም ያልተመዘገቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሰጠው ቀነ ገደብ መሰረት ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ አሳስበዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፤ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደ ባለሥልጣኑ ቀርበው ዳግም እንዲመዘገቡ በጋዜጣ፣ በቴሌቪዠንና ሌሎች አማራጮች ጥሪ መቅረቡን ተናግረዋል።
በድጋሚ እንዲሚዘገቡ ከሚጠበቁት 3 ሺህ 529 ድርጅቶች መካከል የተመዘገቡት 1 ሺህ 723 ሲሆኑ 1 ሺህ 558 ድርጅቶች እስካሁን አልተመዘገቡም ብለዋል።
የባለሥልጣኑ ቦርድ በወሰነው መሰረት ለድርጅቶቹ ተጨማሪ ጊዜ መፈቀዱን ጠቁመው በተሰጠው ጊዜ እንዲመዘገቡ አሳስበዋል።
ከ2013 እስከ 2015 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲት ሪፖርትና ለህልውናቸው ማረጋገጫ የሆኑ ሌሎች ሪፖርቶችን ያቀረቡና ያላቀረቡት ተለይተው ታውቀዋል ብለዋል።
ሪፖርት ላላቀረቡ ድርጅቶች በጋዜጣ በተደረገው ጥሪ መሰረት 800 ድርጅቶች ሪፖርት ሲያቀርቡ 296 ድርጅቶች ግን እስካሁን ሪፖርት አለማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ለእነዚህ ድርጅቶች የመጨረሻ ዕድል ብቻ መኖሩን ጠቁመው፤ ለመጨረሻ ጊዜ የቀረበውን ጥሪ የማይቀበሉ ድርጅቶችን ግን ባለሥልጣኑ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ትነበብ ብርሃኔ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት፣ የተጠያቂነት መርህን መከተል አለባቸው ብለዋል።
ምክር ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምህዳሩ የተሻለ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።
የፍኖት ማህበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ምክክር በጎ አድራጎት ድርጅት ተወካይና የሕግ አማካሪ አያሌው ቢታኔ፤ የተሻሻለው አዋጅ መሸጋገሪያ ድንጋጌዎች ውስጥ ድርጅቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ዳግም መመዝገብ እንዳለባቸው ቢቀመጥም ያልተመዘገቡ ድርጅቶች ከአንድ ዓመት በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል? የሚለው በግልጽ አለመቀመጡ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል።
የኢትዮ ቲንክ ታንክ ግሩፕ ተወካይ ወይዘሮ ማህደር ዳዲ በበኩላቸው እንደ አዲስ የሚቋቋሙ ድርጅቶች የፋይናንስ እጥረት እየገጠማቸው ነው፤ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።