የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል መቀየር አስችሏል-- የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች - ኢዜአ አማርኛ
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል መቀየር አስችሏል-- የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች
አዳማ፤ሮቤ/ ጊምቢ መጋቢት፤18/2016(ኢዜአ)- -በኦሮሚያ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከማገዝ ባለፈ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል መቀየር ማስቻሉን የክልሉ የተለያዩ ዞኖች ግብርና ኃላፊዎች ገለጹ።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በስፋት ከተከናወኑና ውጤታማ ስራ ከተሰራባቸው ዘርፎች መካከል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠቃሽ ነው።
በዚህ ረገድ ውጤታማ ስራ ካከናወኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አንዱ ሲሆን ባለፉት ሶስትና አራት ዓመታት በመቶ ሺዎች ሄክታር የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዚህ ዓመት ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ደርሷል።
በክልሉ በበጋ መስኖ ልማት ሰፋፊ ስራዎችን ከሰሩ ዞኖች መካከል የባሌ፣ የምስራቅ ሸዋና የምዕራብ ወለጋ ዞኖችን መጥቀስ ይቻላል።
ኢዜአ ከሶስቱ ዞኖች የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ቆይታም ዞኖቹ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ከመደገፍ አልፎ ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ መቻላቸውን አረጋግጧል።
የባሌ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልዪ መሀመድ እንደገለፁት፤ በዞኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ውጤት ተገኝቷል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በዞኑ ከ2013 ዓ.ም በ710 ሔክታር መሬት ላይ መጀመሩን ጠቅሰው ዘንድሮ በዞኑ 10 ወረዳዎች በ171 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ለምቶ ይገኛል ብለዋል፡፡
በጥቂቱ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዘንድሮ 1 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል ስንዴ ምርት ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ከለውጡ በኋላ ለስንዴ ምርትና ምርታማነት ዕድገት በተሰጠው ትኩረት በባሌ ምድር የሚገኙ የእርሻ ማሳዎች በበጋም በክረምትም በስንዴ ሰብል እንዲሸፈን መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የሰብል በሽታንና ተባዮችን መቋቋም የሚችልና በአጭር ጊዜ የሚደርስ ምርጥ ዘር በመጠቀም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በዞናችን የማስፋፋት ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የመስኖ ባለሙያ አቶ ጫንያለው ሆርዶፋ በበኩላቸው በ2010 ዓ.ም በ765 ሔክታር መሬት ላይ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ዘንድሮ በ389 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በአመት ከሚገኝ 24 ሺህ ኩንታል ምርት ወደ 16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መሰብሰብ የደረሰ ለውጥ ማየት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
በዞኑ የመስኖ ስንዴ ምርት ለማስፋፋትና የተያዘለትን ግብ ለማሳካት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ከመጨመር ጀምሮ የምርት ማሳደጊያ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በአግባቡ እንዲዳረስ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በቆላማ አካባቢ ያሉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበሩ የ28 ቀበሌ አባዎራዎች ከእርዳታ ወጥተው አምርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በተለይም የቦሰት፣ ፈንታሌና አዳማ ከፊል አርብቶ አደር ወረዳዎች የመስኖ ስንዴ ልማት አኗኗራቸውን እንደቀየረው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተገኙ ተሞክሮዎች በመነሳት የመስኖ ስንዴ በማልማት የምርት መጠንን ማሳደግ እንዲሁም ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ከአርሶ አደሩ ጋር በቅንጅት መስራታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም እምብዛም የመስኖ ልማት ልምድ የሌለበት ምዕራብ ወለጋ ዞንም በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ስራ መስራቱን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈይሳ ሀምቢሳ ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ በ2013 ዓ.ም ከ1 ሺህ 274 ሔክታር በላይ መሬት ላይ ከለማው ስንዴ 26 ሺህ ኩንታል በመሰብሰብ የተጀመረው ስራ ዘንድሮ በ97 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ስንዴ ማልማት ተችሏል።
ከዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርትም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ለመሰብሰብ ታቅዷል ነው ያሉት፡፡
እንደ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎቹ ገለጻ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የአርሶ አደሩን የስራ ባህል ከመቀየር አንጻርም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።