ቀጥታ፡

የሀረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 18/2016(ኢዜአ)፦የሀረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን ለማስጀመር የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የምስራቅ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግሪድ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የሳይት ተወካይ አቶ መኮንን ዓለሙ እንዳስታወቁት ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ቦታ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ተገቢውን ካሳ ለመክፈል የእርሻ መሬት ልኬትና የተክል ቆጠራ ቀደም ብሎ ተከናውኗል፡፡

ይዞታቸው ለፕሮጀክቱ የሚፈለግ 40 የአካባቢው ነዋሪዎች በልኬቱና በቆጠራው መሠረት አስፈላጊውን ካሳ ከፍሎ ለግንባታ ዝግጁ ለማድረግ ከሚመለከታቸው የክልል፣ የወረዳና የአካባቢው መስተዳደሮች ጋር ሰፊ ውይይቶች መደረጋቸውን ተወካዩ አንስተዋል፡፡

የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቱ በሚያርፍበት ቦታ ላይ ከፕላን ጋር ተያይዘው የተነሱ ጥያቄዎች መኖራቸውን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ጉዳዩ በክልሉ ምክር ቤት ታይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሀረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የከተማ ማደስና መልሶ ማልማት ቡድን መሪ አቶ ፈቲ ሁሴን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በከተማዋና በዙሪያው ለሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ለአርሶ አደሮቹ ተገቢውን ካሳ ለመክፈል ከክልሉና ከወረዳ መስተዳድር የተውጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኮሚቴዎች ሲከታተሉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የካሳ ክፍያ መመሪያው በሚያዘው መሠረት በየሁለት ዓመቱ የሚሻሻል መመሪያ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ፈቲ በዚህ ምክንያት ግምቱ እንደዘገየ አስረድተዋል፡፡

አሁን ግን የካሳ ክፍያውን የመጨረሻ ግምት አፅድቆ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ለአርሶ አደሮቹ ክፍያ የሚፈፀምበት የባንክ ደብተር፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች እየተጠናቀቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የሀረር ቁጥር 4 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከሀረር ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቃሊ ቀበሌ ሊገነባ የታሰበ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ልማት ባንክ ፋይናንስ የሚገነባ ሲሆን የምስራቅ ኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ግሪድ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል መባሉን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም