በኢትዮጵያ የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊዮን ደርሷል

358

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የመንግስትና የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊዮን መድረሱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ ስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ በነበረው የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቴሌኮም ዘርፉ የተደረጉ ማስፋፊያዎችና ለውጦችን ዘርዝረዋል።

በዚህም በግልና በመንግስት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የሞባይል አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር 85 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁለቱ የቴሌኮም የአገልግሎት አቅራቢዎች ከ96 ሚሊዮን በላይ ማስተናገድ የሚችል የኔትወርክ አቅም መፍጠራቸውንም ጠቅሰዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 17 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 41 ሚሊዮን መድረሱን ተናግረዋል። 

በመንግስትና በግል አጋርነት በተሰራ ማስፋፊያ 6 ነጥብ 3 ሜጋዋት (አይቲ ሎድ) የመሸከም አቅም ያለው የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቅሰዋል።

ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያነሱት፡፡

የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ የዲጂታል ክፍያን ማሳደግ የተገነባውን መሰረተ ልማት እሴት እንዲጨምር ማድረግ የተቻለበትን አሰራርም አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ  አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና በበኩላቸው በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የበኩሉን ሚና እንዲጫዎት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለማሳካት በጤናው ዘርፍ፣ ስማርት ሲቲ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ግብር፣ በፍትህ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  ጠቅሰዋል።


 

ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ከማድረግ ጎን ለጎን ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንንነት አስተዳደር ዋና ዳሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ናቸው።

የውይይት ተሳታፊዎች በበኩላቸው የዲጂታል አሰራርና አገልግሎትን በማቀላጠፍ፣ ለህብረተሰቡ ተደራሽ በመሆንና ጊዜና ወጪን በመቆጠብ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ አንስተዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ በመሬት፣ግንባታ ፈቃድ፣ ወሳኝ ኩነትና ሌሎች ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማሳለጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ብልጽግና እንዲሁም ዲጂታል ኢትዮጵያን በቀሪዎቹ አመታት እውን ለማድረግ የተጀመሩ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበትም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም