ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ ዓመታት በፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ አሳታፊነት ላይ የተሻለ ለውጥ ይመጣል-ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦  በቀጣዮቹ ዓመታት በፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ አሳታፊነት ላይ  የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።

የባንኩ ገዥ ይህን የተናገሩት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ግምገማ ላይ በነበረው የፓናል ውይይት ላይ ነው።


 

ስትራቴጂው የፋይናንስ ዘርፉን ስራዎች በማዘመንና በማሳለጥ መሰረታዊ በሆነ መንገድ መቀየሩን አብራርተዋል።

የፋይናንስ ዘርፉ በቁጠባ፣ በብድር፣ ኢንሹራንስና ኢንቨስትመንት ለሚያከናውናቸው ተግባራት የዲጂታል ፋይናንስ ስርአት አሰራር አገልግሎትን ቀልጣፋ አድርጓል ነው ያሉት።

በተለይም በፋይናንስ ተደራሽነት፣ ክፍያ ስርአትና አካታችነት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

 ለአብነትም 32 ሚሊዮን የሞባይል ባንክ ተጠቃሚዎችና 42 ሚሊዮን የክፍያ ካርዶች መኖራቸውን ገልጸው ባለፉት 5 ዓመታት የዲጂታል ክፍያ  በ750 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

ይህም በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ፋይናንስ ስርዓቱ አገልግሎት አሰጣጥ በማቀላጠፍና አዳዲስ የዘርፉ ተዋናዮችን በማብዛት በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ይኖራል ብለዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በትግበራ ላይ ከሚገኘው አዋጅ በተጨማሪ በቅርቡ አዲስ የባንክ የፋይናንስ ህግ እንደሚወጣ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት 14 "የፊንቴክ" ኩባንያዎች ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን የውጭ ባንኮች ዘርፍን በሚቀላቀሉበት ወቅት መሰረታዊ ለውጥ እንደሚመጣ ገልጸዋል።

በዚህም ቁጠባን ወደ ኢንቨስትመንት በመቀየር የምጣኔ ሃብት ምርታማነትን በማሳደግ፣ ከሌሎች አገሮች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማምጣትና የፋይናንስ ስርአቱን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ ከቀናት በፊት የተከሰተው ችግር አሰራርን በማሻሻል ሂደት የተከሰተ ችግር መሆኑን ጠቅሰው ብሔራዊ ባንክ የማጣራት ስራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የዲጂታል ፋይናንስ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ የተከናወኑ የገንዘብ ዝውውሮችን መከታተል የሚያስችል  በመሆኑ የሚጠፋ ገንዘብ እንደማይኖር ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም