በኢትዮጵያ የዲጂታል ዘመንን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን በመገንባት ረገድ አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል

281

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዲጂታል ዘመንን ታሳቢ ያደረጉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን በመገንባት ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተገምግሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የዲጂታል አቢዮትን ለማሳካት እያከናወነች ያለውን ተግባር፣ የስትራቴጂው አስፈላጊነት፣ ትግበራና እየተመዘገቡ ያሉ ለውጦችን ዘርዝረዋል።


 

ከዚህም ውስጥ  የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ስትራቴጂው ከሰጣቸው ትኩረቶች አንዱ አካታችነት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍበትን ምቹ ሁኔታ ማመቻቸትና የፈጠራ ባለሙያዎች እንዲበራከቱ በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።  

መንግስት ወጣቶች ቴክኖሎጂ ለገቢ ምንጭነት እንዲያውሉት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም እንዲሁ፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሚፈለገውን እድገትና ለወጥ ለመምጣት ዲጂታል ምጣኔ ሃብት ዋነኛ ምሰሶና ስትራቴጂ ሆኖ መቀየሱን አብራርተዋል።


 

ለዚህ ደግሞ ከዲጂታል ዘመን ጋር አብሮ መሄድ የሚያስችሉ የኃይል፣ የዳታ፣ የዲጂታል መታወቂያና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች በህግ፣ በስትራቴጂና በተቋማት መሰረት እየያዙ መሆኑን አስረድተዋል።

የዲጂታል ዘመን እያደገ ሲሄድ በተቋማት ላይ የሚሰነዘረው የሳይበር ጥቃቶችም እየጨመሩ እንደሚመጡ ገልጸው ከዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል። 

ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ሌሎች ጠንካራ ተቋማት እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ተወዳዳሪ እንድትሆንም ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት የሚሆኑ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቀሪዎቹ ዘመናት የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም