በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ያዘዋወሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ያዘዋወሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ
ደሴ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር ለፀረ ሰላም ኃይሎች ሊያቀብሉ የሞከሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡
በአገር መከላከያ ሰራዊት ኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የ103ኛ ክፍለ ጦር 5ኛ ኮማንዶ ሪጅመንት ዋና አዛዥና የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻምበል ታሪኩ ሻሜቦ እንደገለጹት፤ በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት መያዝ ተችሏል።
ሀያ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ክላሽና ሌሎች መሳሪያዎችን እንደያዙ ነው።
ተጠርጣሪዎቹ በግለሰቦች እጅ መያዝ የሌለባቸው እንደ ብሬንና ስናይፐር የተባሉ የቡድን መሳሪያዎችም በእጃቸው መገኘቱን ጠቁመው፤ በድርጊቱ የተሳተፉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ተጠርጣሪዎች መሳሪያ በማዘዋወርና በመገበያየት ለፀረ ሰላም ኃይሉ በማቀበል ቀጣናውን የግጭት አካባቢ ሊያርጉ እንደነበሩ የገለጹት ሻምበል ታሪኩ፤ "ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ትብብር ሴራቸውን ማክሸፍ ተችሏል" ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠበቆ ከሰራዊቱ ጎን መሰለፉን ተናግረው፤ ይህን የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።