በክልሉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ ልማትን ለማፋጠን የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሚና ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ ልማትን ለማፋጠን የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሚና ይጠናከራል
ቦንጋ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ ልማትን ለማፋጠን የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ሚና እንደሚያጠናክር የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በመተባባር ለኢንተርፕራይዞችና ባለሀብቶች ያዘጋጀውን ስልጠና በቦንጋ ከተማ መስጠት ጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚና መሠረተልማት ዘርፍ አማካሪ ዶክተር ኢንጂነር ምትኩ በድሩ በሥልጠናው ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ክልሉ ለልማት የሚውል ያልተነካ እምቅ አቅም ባለቤት ነው።
በክልሉ ያለን ዕምቅ አቅም በማውጣት ልማቱን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የመካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ሚና ለማጠናከር ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ይህም በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት አምራች ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት እንዲጠቀሙ በማድረግ ምርታማነትን ለመጨመርና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግርን ለማፋጠን ያግዛል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት የኢንተርፕራይዞችን አቅም በመገንባት በእውቀትና ክህሎት እንዲመሩ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አማካሪው፣ ይህን ውጤታማ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ባንኩ በክልሉ ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት በሀገሪቱና በአካባቢው ያለውን አቅም በመጠቀም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናም አቅርበዋል።
ሰልጣኞች በተሰጣቸው ዕድል ተጠቅመው ለኢኮኖሚ ዕድገት ድርሻቸውን እንዲወጡም አማካሪው አሳስበዋል።
በክልሉ 737 መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ ናቸው።
ኢንዱስትሪዎቹ በአካባቢያቸው ያለውን ሀብትና አማራጭ ተጠቅመው በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ቢሮው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የሚስተዋልባቸውን የእውቀትና ፋይናንስ ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የክትትልና ድጋፍ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አቶ ግዛው አስታውቀዋል።
ከባንኩ ጋር በቅንጅት የተዘጋጀው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በሀገር ደረጃ በአራት ዙሮች ከ145 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ስልጠና መስጠቱን የገለፁት በቪድዮ ኮንፈረንስ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው አበራ ናቸው።
ባንኩ ከክልሉ መንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ መጠን ያላቸው የፕሮጀክት ብድርና የሊዝ ፋይናንስ ጥያቄዎችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
"ስልጠናው በክልሉ ባሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ባለሀብቶች ጥያቄ መሠረት መዘጋጀቱ ባንኩ ከዚህ ቀደም ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ለየት ያደርገዋል" ሲሉም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ባንኩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ከፍተኛ ሚና ከግንዛቤ በማስገባት የሊዝ ብድር መዘጋጀቱን አቅማቸውን ለማጠናከርና ተወዳዳሪ ለመሆን ያግዛቸዋል ብለዋል።
ለአምስት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ላይ 670 ኢንተርፕራይዞችና ባለሀብቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።