የኢትዮጵያ የህንፃ ደንብና ደረጃ ማሻሻያ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል- የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የህንፃ ደንብና ደረጃ ማሻሻያ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል- የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ያለውን የህንፃ ደንብና ደረጃ የማሻሻል ስራ በተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሲቪል መሃንዲሶች ማህበር ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ዘላቂ መሰረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችል ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በተለይ ከለውጡ አመታት ወዲህ በርካታ ሜጋ ፕሮጀክቶች በመገንባት ላይ ናቸው ።
እነዚሁ ፕሮጀክቶች የሕብረተሰቡን የልማት ፍላጎት የሚመልሱና ዘላቂነትን ያረጋገጡ እንዲሆኑም በርካታ ተግባራትን እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የህንፃ ደንብና ደረጃ በየጊዜው እየተሻሻለ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ያለውን አለም አቀፋዊ የአየር ሁኔታና የተፈጥሮ ለውጦች ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሻሻለ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሚገነቡ መሰረተ ልማቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ስለሚችል በጥንቃቄ ማከናወን ይገባል ነው ያሉት።
ግንባታዎቹን ዘላቂ በማድረግ ከመጪው ትውልድ አንፃር ቃኝቶ ማካሔድ እንደሚያስፈልግም አያይዘው ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የኮንስትራክሽን ፖሊሲ ዘላቂነትን ያካተተ ባለመሆኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ የማሻሻል ስራዎች እየተከናወነ እንደሆነም ገልፀዋል።
በግንባታው ዘርፍ የጤና ደህንነትና ከባቢን በተመለከተ የህግ ማዕቀፍ በማውጣት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት::
በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለው የአየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነት መጨመርን ለመከላከል በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል መሃንዲሶች ማህበር ፕሬዝዳንት ዮናስ አያሌው፤ባለሙያዎች የሚያካሒዷቸው ግንባታዎች ከዲዛይን ጀምሮ ጥራትን ብቻ ሳይሆን ዘላቂነታቸውን የሚያረጋግጡ መሆን አለባቸው ነው ያሉት።
ውይይቱ የምህንድስና ባለሙያዎች የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ሲያካሒዱ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ አድርገው እንዲያከናውኑ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፕሮጀክት አገልግሎት ፅሕፈት ቤት የዩ ኤን ኦፓስ የአፍሪካ ህብረት ተወካይና የኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ ዳይሬክተር ወርቅነሽ መኮንን፤ ውይይቱ የግንባታ ስራዎችን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር አስተሳስሮ መሔድ በሚቻልበት መንገድ ላይ እንደሚካሔድ ጠቁመዋል።
ከከተሞች መስፋፋት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የአየር ጠባይ ለውጥና ቴክኖሎጂ መሻሻል ጋር ተያይዞ በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመለየት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል ።
ለሁለት ቀናት የሚካሔደው ውይይት በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን በመለየት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች ይነሱበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ሲቪል መሃንዲሶች ማህበር ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፕሮጀክት አገልግሎት ፅሕፈት ቤት (ዩ ኤን ኦፓስ) ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁትም ተገልጿል።