ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ ተወስዶ ያልተመለሰውን ቀሪ ገንዘብ ለማስመለሰ ወደቀጣይ እርምጃዎች እንደሚገባ ገለፀ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ ተወስዶ ያልተመለሰውን ቀሪ ገንዘብ ለማስመለሰ ወደቀጣይ እርምጃዎች እንደሚገባ ገልጿል።

በዛሬው እለት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለፁት ባንኩ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት በተፈጠረ ችግር አላግባብ ከተወሰደበት 801,417,747.81 ብር ውስጥ 622 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር (78 በመቶ) እስካሁን ተመልሷል።

ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው 168,609,283.7 ብርም ለመመለስ ቃል መገባቱን አስታውቀዋል።

አቶ አቤ ያለአግባብ በ567 ግለሰቦች የተወሰደውን ቀሪ 9,838,329.12 ብር ለማስመለሰ ባንኩ ወደቀጣይ እርምጃዎች እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ገንዘቡን ያልመለሱት ግለሰቦች እንደሚታወቁ ጠቅሰው፤ ከተወሰደው ገንዘብ ውስጥ አንድ ግለሰብ የወሰደው ከፍተኛው ብር 304 ሺህ ብር መሆኑንና ከአምስት ብር በታች የወሰዱም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

አቶ አቤ ባንኩ በቀጣይ ገንዘቡን የወሰዱትን ግለሰቦች የስም ዝርዝር ሂሳባቸው ባለበት ዲስትሪክት እና ቅርንጫፍ እንዲሁም በባንኩ ማኅበራዊ ሚዲያ በመለጠፍ እስከ ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ እንዲመልሱ ይደረጋል ብለዋል፡፡

እስከተጠቀሰው ቀን ድረስ ገንዘቡን በማይመልሱ ግለሰቦች ላይ ጉዳዩን እስከ ፍርድ ቤት ድረስ የመውሰድ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸውን ከንግድ ባንክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም