የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ወሳኝ ርምጃዎችን ተራምደናል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 

272

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ወሳኝ ርምጃዎችን ተራምደናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025" ለፈጠራ ሰዎች ድጋፍ በማስገኘት እና ለዲጂታል ጉዞ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በዲጂታል ኢኮኖሚ እንድንበረታ ዐቅም ሆኖናል ብለዋል። 

ዛሬ ያደረግነው የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ተግዳሮቶቻችንን ለመፈተሽ ብሎም የጉዟችንን ስኬታማ እጥፋቶች ለማክበር ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉም አክለዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ወቅት ለዕቅዱ መነሾ የሆኑ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን ማብራሪያ መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም በኢትዮዽያ የሀገር በቀል ለውጥ አጀንዳ፣ ብሔራዊ የ10 ዓመት ዕቅድ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች ዕቅድ፣ የአፍሪካ ኅብረት አህጉራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ የመነጨው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በኢትዮጵያ ፈጠራ እና የእውቀት መሠረት ያለው ኢኮኖሚ ለማደርጀት ያለመ ነው ብለዋል። 

በዚሁ ውይይት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ዲጂታል ጉዞ የተገለጠበትን መንገድ አፅንዖት ሰጥተው አንስተዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም