ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 622 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 622 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር (78 በመቶ) ማስመለስ መቻሉን ገልጿል።

ከሲስተም ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት በተፈጠረ ችግር ምክንያት 801 ሚሊዮን 417ሺህ 747 ነጥብ 81 ብር ያላግባብ ተወስዶ እንደነበር ባንኩ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ያሳወቀ ሲሆን፣ 622 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉ ተገልጿል፡፡


ከባንኩ አላግባብ የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለሰ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለህብረተሰቡ ለማሳወቅ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደገለፁት ችግሩ በተከሰተበት ቀን ከምሽቱ 3፡38 ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 8፡45 ድረስ በ25,761 ሂሳቦች አማካኝነት 238‚293 ህገወጥ ግብይቶች ተከናውነዋል፡፡

አቶ አቤ ችግሩ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ የባንኩን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ለተወሰኑ ሰዓታት በማቆም እና ችግሩ በተከሰተበት ሰዓት በገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ ሂሳቦችን በማገድ የጉዳት መጠኑን መቀነስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
 
ባንኩ በቀጣይ በወሰዳቸው እርምጃዎች ያላግባብ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከተደረገባቸው እና በቂ ገንዘብ ከነበራቸው ከ10,727 ሂሳቦች ቀጥታ ብር 44,668,232.41 ተመላሽ የተደረገ ሲሆን፣ ከ15,008 ሂሳቦች ደግሞ በከፊል ማለትም ብር 205,805,340.9 ብር ተመላሽ ተደርጓል፡፡

በጉዳዩ ተሳትፎ የነበራቸው 9,281 ያህል ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ ብር 223,475,369.31 ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት የመለሱ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አቤ፣ 5,160 ደንበኞች ደግሞ በከፊል ማለትም ብር 149,021,191.37 መመለሰቻውን አሳውቀዋል፡፡ 

አላግባብ ከወሰዱት ብር 9,838,329.12 እስካሁን ምንም ያልመለሱ 567 ግለሰቦች መኖራቸውንም ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸውን ከባንኩ ማህበራዊ ትስስር  ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


አቶ አቤ ያላግባብ የወሰዱትን ገንዘብ በፈቃደኝነት የማይመልሱ ግለሰቦችን በተመለከተ ቀደም ሲል ባንኩ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አስፈላጊውን ተግባራት በቅደም ተከተል በማከናወን ጉዳዩ ለህግ አካል እንደሚቀርብ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም