ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት ይሰራል

ቡታጅራ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተመዘገበ ያለውን የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምርታማነት በክልሉም ለማስቀጠል እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

ክልል አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት የኢንቨስትመንት ንቅናቄ መድረክ በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር አባስ መሐመድ እንዳሉት እንደ ሀገር በአዲስ ዕሳቤ የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲነቃቃ እያደረገ ነው።

እንደሀገር በዘርፉ እየተመዘገበ ያለውን ምርታማነት በክልሉም አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ዘርፉ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በመሻገር አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የፌዴራል መንግሥት አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል።


 

በዚህም አምራች ዘርፉ በሙሉ አቅሙ እንዳያመርት ያደረጉትን ማነቆዎች መንግስት በመፍታት አቅሙን አሟጦ እንዲያመርት እገዛ እያደረገ መሆኑንም ሃላፊው አስረድተዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እያደረገ ያለው ሽግግር አዝጋሚ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አባስ የክልሉ መንግሥት ችግሮችን ለይቶ በመፍታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መድረኩ በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮችን ለይቶ በመምከር አቅጣጫ ለማስቀመጥ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሞሎ፣ የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ፣ የቢሮ ሃላፊዎች፣ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።

ከመድረኩ በተጓዳኝ በክልሉ የኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይም ተከፍቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም