ወደ ውጭ ሀገር ለስራ የሚጓዙ ዜጎች ህጋዊውን መንገድ በመከተል ከሚደርስባቸው ችግር ራሳቸውን መከላከል አለባቸው

ድሬዳዋ፤ መጋቢት 17/2016 (ኢዜአ)፡- ወደ ውጭ  ሀገር ለስራ  የሚጓዙ ዜጎች ህጋዊውን መንገድ በመከተል ከሚደርስባቸው ችግሮች ራሳቸውን መከላከል እንደሚገባቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል አሳሰቡ።

 ሚኒስትሯ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተዋቀረው ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት የዜጎችን የስራ ጥያቄ በተሟላ መንገድ መመለስ በሚችል አኳኋን ላይ ነው፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ዜጎችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ይበልጥ ተደራሽ  ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎን በአገሪቱ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ክህሎት መር የስልጠና ሪፎርምን እንዲተገብሩ በማድረግ ተወዳዳሪና በክህሎት የበለፀገ ብቁ ባለሙያ በመፍጠር ጅምር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

እነዚህን የሰለጠኑ ስራ አጥ  ዜጎች  በአገርና በውጭ አገራት  የስራ ባለቤት ለማድረግ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ የተገኙ ውጤቶች መኖራቸውን ነው ሚኒስትሯ የገለፁት።

ወደ ውጭ አገራት ለሥራ ለሚጓዙ ዜጎች በኢትዮጵያ የገበያ መረጃ ስርዓት መሠረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ ይህ አሰራር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት በመተግበሩ ቀደም ሲል ጥያቄ ሲነሳባቸው ለነበሩት የክፍያ መብዛትንና የፓስፖርት አሰጣጥ መጓተትን  ማስቀረት አስችሏል።

በመሆኑም ዜጎች የተዘረጋውን ህጋዊ መንገድ  በመጠቀም ከህገ ወጥ መንገድና  ጉዞ በመታቀብ በህይወት፣ በገንዘብና በደህንነት ላይ ከሚደርሱ ችግሮች  ራሳቸውን መከላከል እንደሚገባቸው ነው ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ያሳሰቡት።

በህገ ወጥ ስራ የተሰማሩትን ወንጀለኞች ህብረተሰቡ የማጋለጥ  ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበትም በማሳሰብ።

በዘንድሮ  በጀት ዓመት  ሰባት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በአገር ውስጥ ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰው፤  ለ243 ሺህ ዜጎች ደግሞ በተለያዩ የውጭ አገራት የስራ ዕድል እንዲፈጠር ተደርጓል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ  ከፍተኛ የዲፕሎማሲና የድርድር ስራዎች በመስራት የሚካሄደው የውጭ አገራት የስራ ስምሪት በርካታ ጥቅሞች አሉት።

በተለይም ለፍተው ባዶ እጅ እንዳይመለሱ የቁጠባ ሥርዓት ከቴሌብር ጋር መዘርጋቱን ገልጸው፤ ይህም ዜጎቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱ ጥሪት ይዘው በመምጣት እስከ ኢንቨስተርነት የሚያደርሳቸው አቅም እንዲገነቡ ያስችላል ብለዋል።

የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ፣ ለሙስና የነበረን ተጋላጭነት በመቀነስ፣ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድም ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም