ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስፖርተኞች ባስመዘገቡት አኩሪ ውጤት ኮርታባቸዋለች

257

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 17/2016(ኢዜአ)፦በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስፖርተኞች ፈታኙን ሞቃታማ የአየር ንብረት በመቋቋም ባስመዘገቡት  አመርቂ ውጤት ኢትዮጵያ ኮርታባቸዋለች ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ። 

በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳን ጨምሮ በሚኒስቴሩ የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉና ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮችና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል። 

ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና የተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ9 የወርቅ፣ 8 የብር፣ 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ስፖርተኞቹ በጋና የነበረውን ሞቃታማ አየር በመቋቋም ያስመዘገቡት ውጤት የሚያኮራ ነው ብለዋል።

በአትሌቲክስ የተመዘገበው ውጤትና የተገኙ ሜዳሊያዎች ለቀጣይ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለስፖርቱ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የባህልና የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጨዋታዎች በዘጠኝ ስፖርቶች ተሳትፋ ከአትሌቲክስ በተጨማሪ በብስክሌትና ቦክስ ያስመዘገበችው ውጤት በሌሎች ስፖርቶች ላይ ከተሰራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ለዚህም መንግስት ከብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

በአህጉራዊው ስፖርታዊ ሁነት የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በሚገባ ማስተዋወቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ጨዋታዎች የተመዘገበው ውጤት በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስንቅና አቅም እንደሚሆን ነው አምባሳደር መስፍን የገለጹት።


 

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በአፍሪካ ጨዋታዎች ከተመዘገቡ 22 ሜዳሊያዎች 18ቱ በአትሌቲክሱ የተገኘ መሆኑን ገልጻ የተገኘው ውጤት አትሌቶች አስቸጋሪውን የአየር ንብረት ተቋቁመው ያገኙት እንደሆነ ተናግራለች።

በተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የስፖርት ሁነቶች ላይ በአትሌቲክሱ አመርቂ የሚባል ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቅሳለች።

እንደ አፍሪካ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች በምትሳተፍበት 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክሱ የተሻለ ውጤት ለማግኘት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብላለች።

በ13ኛው አፍሪካ ጨዋታዎች በ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች እርምጃ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ስንታየሁ ማስሬና በ3 ሺህ ሜትር ሴቶች መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ሎሚ ሙለታ በጋና የነበረው ሞቃታማ የአየር ንብረት ፈታኝ ቢሆንም ጫናውን በመቋቋም ሜዳሊያ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በሚኖሩ ውድድሮች ላይ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ካገኘቻቸው በተጨማሪም በቦክስ ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ እንዲሁም በብስክሌት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም