ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ይዞ የሚያስተዳድረው የቶጎ ሎሜ "አስካይ" አየር መንገድ ውጤታማ ሆኖ ቀጥሏል - አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ ይዞ የሚያስተዳድረው የቶጎ ሎሜ "አስካይ" አየር መንገድ ውጤታማ ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

ሌሎች የአፍሪካ አገራትም አየር መንገዶቻቸውን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋራ በሽርክና ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ መዳረሻዎቹን ለማስፋት፣ የአውሮፕላን ቁጥሮችን ለመጨመርና እንዲሁም ሌሎች የሥራ ዘርፎችን ለማጠናከር እየሰራ ነው።

አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ ውጭ በአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን በማቋቋምና በማስተዳደር ያለውን ድርሻ አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው አሁን ላይ አየር መንገዱ 22 ነጥብ 46 በመቶ ድርሻ በመያዝ የሚያስተዳድረው ''አስካይ'' አየር መንገድ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ይህም አየር መንገድ አሁን ላይ ትርፋማ ሆኖ በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነትም ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት አየር መንገዱ ከፍተኛ የተባለውን ከ40 ሚሊየን ዶላር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ነው የገለጹት። 

ይህም ብቻ ሳይሆን አየር መንገድ በአሁኑ ወቀት በ14 አውሮፕላኖች የአየር ትራንስፖርት እየሰጠ መሆኑን ተናግረው በቀጣይም ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለማስገባትና አገልግሎቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

አስካይ አየር መንገድ አሁን ለደረሰበት የእድገት ደረጃ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ልምድና ተሞክሮ በማጋራት ለአየር መንገዱ እድገት በቁርጠኝነት በመሥራቱ መሆኑን ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው  ያስረዱት።   

የቶጎ አየር መንገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰራቸው የትብብር ሥራዎች ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ በቀጣይ ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ጠቁመዋል። 

ሌሎች የአፍሪካ አገራትም አየር መንገዶቻቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብር ለመሥራት ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።  

በቅርቡ የኢኳቶሪያል ጊኒ መንግሥት አየር መንገድ እንዲቋቋምላቸው በጠየቁት መሠረት፤ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 49 በመቶ የኮንጎ መንግሥት ደግሞ 51 በመቶ ድርሻ ይዞ ለማቋቋም ሥምምነት መደረጉን ተናግረዋል።

የአፍሪካ አየር መንገዶች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በባለድርሻነት ይዞ እንዲያቋቁምና እንዲያስተዳድርላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ማሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለመፈፀም ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም