ቀጥታ፡

የክልሉን ፖሊስ ወንጀል የመከላከል አቅምን ለማጎልበትና የአመራር ክህሎትን ለማሳደግ ድጋፍ ይደረጋል-ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ 

መቀሌ፤ መጋቢት 16/2016 (ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልልን ፖሊስ ወንጀል የመከላከል አቅምን ለማጎልበትና የአመራር ክህሎትን ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር ''ለውጤታማ የፖሊስ አገልግሎት የአመራር ሚና'' በሚል መሪ ሃሳብ ለክልሉ የፖሊስ አመራር አባላት በመቀሌ ዛሬ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ጀኔራል መስፍን አበበ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የትግራይ ክልልን  የፖሊስ ተቋምና የፖሊስ አገልግሎት ወደ ነበረበት ለመመለስ የስነ ልቦናና የአቅም ግንባታ ስልጠና አስፈላጊ ነው፡፡


 

''በህዝባዊ ወገንተኝነት ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን የፖሊስ ሚና መተኪያ የለውም'' ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራሉ፣ ስልጠናው የፖሊስ ተቋሙንና የፖሊስ አባላትን አቅም በማሳደግ ህዝባዊ አገልግሎቱን ለማስቀጠል ያግዛል ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የዲሞክራታይዜሽንና ያልተማከለ አስተዳደር ሴክሪቴሪያት ሃላፊ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በበኩላቸው የፖሊስ አቅም ካልተጠናከረ በወንጀል መከላከል ስራዎች ውጤታማ መሆን አይቻልም ብለዋል።


 

በአሁኑ ወቅት ለፖሊስ አመራር አባላት የሚሰጠው ስልጠና አቅማቸውን ለማጎልበትና የአመራር ክህሎትን ለማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው የተቀናጀ የፖሊስ አገልግሎት በማጠናከርና ሙያዊ አቅም በማሳደግ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርላቸው የተናገሩት ደግሞ የስልጠናው ተሳታፊዎች የሀገረ ሰላም ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አረጋዊ ገብረመድህንና የአጽቢ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ጌታቸው ሃይለማርያም ናቸው። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም