በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች የእምቦጭ አረምን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የማስወገድ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

407

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 16/2016 (ኢዜአ)፦ በስምጥ ሸለቆ ሦስት ሐይቆች ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በህብረተሰቡ ተሳትፎ የማስወገድ ሥራ እያከናወነ መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስምጥ ሸለቆ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዴቢሶ ዴዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በቤዚኑ አስተዳደር ስር ከሚገኙ ሰባት ትላልቅ ኃይቆች ውስጥ በሦስቱ ላይ የእምቦጭ አረም ተከስቷል።

በዝዋይ-ደንበል ሻላ፣ በአባያ እና በጫሞ ሐይቆች ላይ የእምቦጭ አረሙ 9ሺህ 305 ሄክታር በሚያካልል የውሃ አካላት ላይ መስፋፋቱን ገልጸው፣ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የእምቦጭ አረም በሐይቆቹ እና በብዝሃ ህይወት ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የእምቦጭ አረምን በማስወገዱ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ኢትዮዽያ ክልሎች ያሉ ባለድርሻ አካላት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እንዲሁም አረሙ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የውሃ ተጠቃሚ የሆኑ ባለሀብቶችን ጭምር በማሳተፍ አረሙን ከውሃ አካላቱ ላይ ለማስወገድ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በተለይ በዝዋይ ደንበል-ሻላ ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ሥራዎችን በመቀመር በአባያ እና ጫሞ ሐይቆች ላይ አረሙን ለማስወገድ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊ አመልክተዋል።


 

በዚህ ዓመትም በሦስቱ ሐይቆች በ1ሺህ 672 ሄክታር የውሃ አካል ላይ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ የተከናወነው አፈጻጸም ውጤታማ ነው ብለዋል።

አቶ ዴቢሶ እንዳሉት፣ በአባያ እና ጫሞ ሐይቆ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም የማስወገዱ ሥራ አሁንም ተገቢ ትኩረት የሚፈልግ ሲሆን በሥራውም ህብረተሰቡን በተደራጀ መልኩ ማሳተፍ ይገባል። 


 

በደቡብ ኢትዮዽያ ክልል የጋሞ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ልማት ጽህፈት ቤት የብዝሀ ሕይወት ቡድን መሪ አቶ ጋምቡራ ጋንታ በበኩላቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በአባያና ጫሞ ሐይቆች ላይ የእምቦጭ አረም ከተከሰተ ጀምሮ በህዝብ ንቅናቄ አረሙን ለማስወገድ እየተሰራ ነው።

"ሆኖም አረሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና የመከላከል ፍጥነታችንን እየተፈታተነው በመሆኑ ሐይቁን እየጎዳው ይገኛል" ብለዋል።

"እምቦጭን የመከላከል ሥራው በካፒታል ፕሮጀክቶች ከመደገፍ ባለፈ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ወጣቶችን በማሰልጠን ለመከላከል እየተሰራ ነው።" ሲሉም ገልጸዋል።

በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ የፉራ ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ፍፁም አባተ አባያ ሐይቅ ለአካባቢው ህብረተሰብ ለመስኖና ዓሣ ልማት እንዲሁም ለእንስሳት እርባታ ጥቅም እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።


 

"ሐይቁ በእምቦጭ መወረር ከጀመረ ወዲህ የውሃ መጠን እና የዓሣ ምርት እየቀነሰ መጥቷል" ያሉት ሊቀመንበሩ፣ የእምቦጭ አረሙን ለመከላከል ህብረተሰቡን በመሳታፍ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የላንቴ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታሩኩ ብሩ በበኩላቸው፣ አባያ ሐይቅ ለአካባቢው ነዋሪው በርካታ ጥቅም እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሐይቁ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ በሚደረግ ዘመቻ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

እምቦጭን ለማጥፋት በህብረትና በአንድነት እያከናወኑት ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም አረሙ እንዳይስፋፋ በሚከናወን ዘመቻ ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም