ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ስርአት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ሁሉንም ያሳተፈ የግንዛቤ ማስፋት ስራ ትኩረት ተሰጥቶታል

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አካታች፣ ጤናማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ስርአት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ሁሉንም ያሳተፈ የግንዛቤ ማስፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የፋይናንስ ተቋማትን የቁጠባ፣ ብድር፣ የዲጂታል ፋይናንስ፣ የኢንሹራንስና ሌሎችም ላይ የአገልግሎትና አሰራር ማሻሻያ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል።

በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርአት ሰፊውን አርሶ አደር አሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ደንበኞች ጥበቃና እውቀት ተጠባባቂ ዳሬክተር ሙኽዲን ሺፋ፤ በኢትዮጵያ ሰፊና አካታች የፋይናንስ ስርአት የመዘርጋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የዜጎችን የፋይናንስ አገልግሎት ግንዛቤ ማሳደግ አካታች የፋይናንስ ስርአት ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አካታች፣ ጤናማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የፋይናንስ ስርአት ለመዘርጋት ሁሉንም ያሳተፈ የግንዛቤ ስራ በስፋት መከናወን አለበት ብለዋል።

በዚህ ረገድ የወጣቶች፣ የሴቶችንና በተለይም የገጠሩን ማህበረሰብ ትኩረት ያደረገ ብሔራዊ የፋይናንስ ትምህርት እስትራቴጂ እኤአ ከ2021 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።          

በተከናወኑ በርካታ የማሻሻያ ስራዎች ከአምስት አመታት በፊት የነበረው ዝቅተኛ የፋይናንስ ተደራሽነት አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

የፋይናንስ አካታችነት በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው ይበልጥ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም ተናግረዋል።       

የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ እውቀትና ክህሎት በማሳደግ ውጤታማ ለማድረግ የማስተማሪያ ማኑዋል መዘጋጀቱን ጠቅሰው በቀጣይ ለሴቶችና የገጠሩ ህብረተሰብ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትና ሌሎችም የሚሰጡትን የፋይናንስ ትምህርት በመከታተል፣ የሙያዊ እገዛ በማድረግና በማስተባበር አካታች የፋይናንስ ስርአትን እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም የገንዘብ ተቋማትና ሌሎች አጋር አካላት ለፋይናንስ ትምህርት ትኩረት በመስጠት ደንበኞች በቂ እውቀትና ችሎታን ተጠቀምው ትክክለኛ የፋይናንስ ውሳኔ እንዲኖራቸው የማብቃት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም