የዲጂታል ግብይትን ለማሳለጥ መሠረተ-ልማትን ከማስፋት ባለፈ ዘርፉ የሚመራበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ግብይትን ለማሳለጥ መሠረተ-ልማትን ከማስፋት ባለፈ ዘርፉ የሚመራበትን አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይትን ለማሳለጥ መሠረተ-ልማትን ከማስፋት ባለፈ ዘርፉ የሚመራበት የህግ ማእቀፍ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግብይት ምርትና አገልግሎቶችን ኢንተርኔት በመጠቀም ወይም በሌሎች የዲጂታል አማራጮች በፍጥነት፣ ባነሰ ወጪ ማከናወን የሚቻልበት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መሆኑ ይታወቃል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ደግሞ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ማሳለጥና ማስፋፋት የግድ ይላል።
የአፍሪካ ሕብረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ጠንካራ አህጉራዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
የአህጉሪቷ ዜጎች በስፋት የዲጂታል አገልግሎትና ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግም ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፤ ለዚህም ሰፊ መሠረተ-ልማት መገንባት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል።
በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ስትሆን፤ በተለይም የዲጂታል አገልግሎት፣ የግብይትና ሌሎችም በመተግበር ላይ ናቸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ፤ አሁን ላይ ዘመኑ የዲጂታል ዓለም በመሆኑ ሀገራት በዚሁ መንፈስ መሥራትና በፍጥነት መጓዝ ያለባቸው መሆኑን ይናገራሉ።
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ጥረቶች ትልቅ ተስፋ የሰነቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁለንተናዊ ጥረትና ትብብርን የሚሹ ናቸው ብለዋል።
የዲጂታል ዓለም የውድድር መድረክም በመሆኑ የሴክተሩን መሠረተ-ልማት ማሟላትና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይትን ለማሳለጥ መሠረተ-ልማትን ከማስፋት ባለፈ ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የዲጂታል ግብይት ከሀገርም ባለፈ ቀጣናዊና አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ለማሳለጥ እንዲሁም ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠርና ወንጀልን ለመከላከልም ጠቃሚ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ስዩም መንገሻ፤ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ማሳለጥ፣ አስቻይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣የመረጃ አስተዳደር (ፖርታል) ልማትና ሌሎችም ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ እነዚህንና ሌሎችም ግቦች መቀመጣቸውን ጠቅሰው፤ ዕቅዱን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የዲጂታል መታወቂያ፣ የመረጃ መረብ ደኅንነት እየሰራቸው ያሉ መሠረተ-ልማቶች የመሳሰሉ አስቻይ ሁኔታዎች መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ከመንግሥት በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ አዳዲስ የዳታ ማዕከሎች እየተገነቡ መሆኑን ገልፀዋል።
ከ520 በላይ የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ኤሌክትሮኒክ መቀየር መቻሉን፣ ከኢ-ኮሜርስ ጋር ተያይዞ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢ-ኮሜርስ የጭነት አገልግሎት ማዕከል የዚህ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።
ከዲጂታል ግብይት ጋር ተያይዞ የሚኖሩ ስጋቶችን ለመቀነስ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለያዩ የሶሻል ሚዲያ አማራጮች ግብይቶች እየተፈፀሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሕጋዊ አሠራር ሥርዓት ተግባራዊነት በቀጣይ ምዝገባ የማካሄድ ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።