ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ የኦሮሚያ አካባቢ ባሉ ወረዳዎች ለሀገራዊ ምክክር የማህበረሰብ ተወካዮች ልየታ ማካሄድ ጀመረ

ጅማ፤መጋቢት 16/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ባሉ 114 ወረዳዎች የማህበረሰብ ተወካዮች የሚለይበት መድረክ ዛሬ በጅማ በማካሄድ ላይ ነው።

ኮሚሽኑ ዛሬ የጀመረውና ፍትሃዊ ፣ተዓማኒ እና አካታች ሀገራዊ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉትን የማህበረሰብ ተወካዮች የሚለዩበት መርሃ ግብር ለ10 ቀናት የሚቆይ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያም በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶችን በመወያየትና በመነጋገር ለመፍታት ያለሙ ሥራዎችን እያከናወነ  ነው።

በዚህም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ችግሮችን በንግግርና በውይይት የሚፈቱበትን  ባህል ለማሳደግ  መሆኑን አስረድተዋል።

በሀገራዊ ምክክር ችግሮችን በመለየትና በተለዩ ልዩነቶች ላይ በመነጋገር መፍትሄ ያስገኛል የሚል እምነት እንዳላቸውም ኮሚሽነር መላኩ  ገልጸዋል።


 

ማህበረሰቡን ወክለው የሚመረጡ አካላትም "የሀገራችንን ችግር ከመፍታት አኳያ ትልቅ ሀገራዊ አደራ የተጣለባቸው መሆኑን ተገንዝበው ለሰላማዊ ድል መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ተወካዮችን የመለየት ስራው በኦሮሚያ ክልል በአራት ክላስተሮች ተከፍሎ  በአዳማ፣ በጅማ ፣በሐረርና በሻሸመኔ ከተሞች  እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታና ቀረጻ አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ  በበኩላቸው ኮሚሽኑ  የሚያካሂደው ምክክርና ውይይት ግልጽ፣ ሁሉን አካታችና እውነተኛ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የተለያዩ ጥያቄዎች ያላቸው አካላት ወደ  ውይይት እንዲመጡ ማበረታታትና ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ከሌሎች  አካላት ጋር ተቀናጅቶ  እየሰራ መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በዚህ የተወካዮች ልየታ መርሃ ግብር ላይ ከሰባት ዞኖች ባሉ ወረዳዎችና ከአራት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ  የኅብረተሰብ  ክፍሎች መሳተፋቸውን አስረድተዋል።

ከየወረዳው ከሚቀርቡት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከልም ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የሚያቀርቡ ተወካዮች እንደሚመረጡ ተመላክቷል።

በመርሃ ግብሩ ትክክለኛ፣ ተዓማኒና ወካይ ተሳታፊዎችን ለመለየት ከፖለቲካ ፖርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከአባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች፣ ከፍትህ አካላት፣ ከሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ተወካዮቹ ከጅማ፣ቡኖ በደሌ፣ኢሉባቡር፣ቄለም ወለጋ ፣ሆሮ ጉድሩ፣ምእራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች እንዲሁም የጅማ፣ የአጋሮ፣ የመቱና ነቀምቴ ከተሞች የመጡ መሆናቸውም ተገልጿል።

ከጅማ ዞን ወረዳዎች የማና ወረዳ ሴቶችን  ወክለው የተሳተፉት ወይዘሮ ነጃት ሐፊዝ  እንዳሉት  ከወረዳቸው የተመረጡ  10 ሰዎች መካከል ሁለቱን ለመለየት መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የጅማ ከተማን ወክለው የተሳተፉት ዶክተር ከተማ ኤጄሬ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች  ለማካተት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መልካም ጅማሮ ብለውታል።

ችግሮቻችንን ለመለየትና ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት እየተሰራ ያለው ሂደት አዎንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ  ተስፋ አደርጋለሁ  በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም