ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልዑክ በ148ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በ148ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

148ኛው የኅብረቱ ጉባኤ "የፓርላማ ዲፕሎማሲ፡ ለሰላምና መግባባት ድልድይ መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እ.ኤ.አ ከመጋቢት 23 እስከ 27 ቀን 2024 ድረስ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

አቶ አገኘሁ ተሻገር በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የጉባዔው መክፈቻ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል።

በዓለም ላይ የሚታየውን የሰላምና ፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የፓርላማ አባላት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንዲችሉ ጉባኤው በወሳኝ ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ሲሉም አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

በጉባኤው የፓርላማ አባላት በቀጣይ ቀናት በሚኖራቸዉ ውይይት፤ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚያስችሉ ሀሳቦች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ጥሩ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ግጭቶችንና ጦርነቶችን ለማስቆም፤ ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በተጨማሪ የፓርላማ አባላት ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ቀጠናውን በኢኮኖሚ ማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን በማስታወስ፤ ኢትዮጵያ በቀጠናው ይህንን ለመፍጠር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ ስራዎችን እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር መድረክ ማመቻቸትን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተቱ በርካታ ውይይቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል።

 

አፈ ጉባኤው በሩሲያ ፌዴሬሽን በተዘጋጀው በብሪክስ አባል ሀገራት አፈ ጉባኤዎች መድረክ ላይ በመሳተፍ፤ የአባል ሀገራት የፓርላማ ህብረት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ የበኩሏን ተሳትፎ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

በአቶ አገኘሁ ተሻገር በተመራው የኢትዮጵያ የልዑክ ውስጥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጂጌ፣ እና ሌሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች፣ እንዲሁም በጄኔቫ የኢፌዲሪ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ፀጋአብ ከበበውን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም