በህገ ወጥ መንገድ ተጓጉዞ ለፅንፈኛው ሊደርስ የነበረ ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ ተጓጉዞ ለፅንፈኛው ሊደርስ የነበረ ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት ተያዘ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016 (ኢዜአ)፦ የባህርዳር -ጎንደር ኮማንድ ፖስት በህገ ወጥ መንገድ ተጓጉዞ ለፅንፈኛው ሊደርስ የነበረ ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት ከነ አዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር አውሏል።
የኮማንዶና አየር ወለድ ክፍለጦር ሻምበል አዛዥ ምክትል መቶ አለቃ ደጀኔ አበባው መነሻውን ጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ያደረገው ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይት ባህርዳር ቀበሌ 14 ከነ አዘዋዋሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
የፅንፈኛው ተላላኪ የሆኑት ምንይሉ መንግስቴና ደረጄ መርሻ የተባሉ የጎንደር ከተማ ቀበሌ 18 ነዋሪዎች ዘጠኝ ሺህ የሽጉጥ ጥይቱን በህገ-ወጥ መንገድ ከጎንደር ወደ ባህርዳር ቀበሌ 14 ልዩ ስሙ ልደታ ሰፈር ጥይቱን ተቀብሎ ለፅንፈኛው ኃይል ለሚያደርሰው ለአየነው ፀሐይ ጨለማን ተገን አድርገው ሲያስረክቡ ከምሽቱ 3:30 ላይ በኮማንዶና አየር ወለድ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የፅንፈኛውን ህልም የማምከንና ዘራፊውን ቡድን የመደምሰስ ተልዕኳችንን በማጠናከር የባህርዳር ከተማና አካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ዝግጁነታችን ከመቼውም ጊዜ የላቀ ነው ሲሉ ሻምበል አዛዥ ምክትል መቶ አለቃ ደጀኔ አበባው ተናግረዋል።
እርጥቡ ምስጋናው ከሚባል ባለሃብት ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው የሚናገሩት የህገ-ወጥ ጥይት አዘዋዋሪዎች ከጎንደር ባህርዳር እሰከሚገቡ ድረስ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ባጃጅ ብቻ ሲጠቀሙ እንደነበሩና ጥይቱን ለመጨረሻው የፅንፈኛው ተላላኪና አቀባይ አየነው ፀሐይ በማስረከብ ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።