በኮሪያዋ ኡልሳን ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በኮሪያዋ ኡልሳን ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ይሰራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው ኡልሳን ከተማ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚሰራ ተገለጸ።
በደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከኡልሳን ከተማ ከንቲባ ኪም ዱ-ጂየም ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በኢትዮጵያ ማፍሰስ በሚችሉበት እና ከተማዋ ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ጠንካራ የእህትማማችነት ግንኙነት መመስረት በምትችልበት ሁኔታዎች ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኮሪያ ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰው ግንኙነቱ በተለይ በከተሞች ደረጃ በሚደረግ የልምድ ልውውጥና ኢንቨስትመንት ሊጎለብት ይገባል ብለዋል።
አምባሳደር ደሴ አክለውም ከንቲባው በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እንዲያበረታቱም ጠይቀዋል።
የኡልሳን ከንቲባ ዱ-ጂየም ደቡብ ኮሪያ ባሳለፈችው አስቸጋሪ ወቅት ኢትዮጵያ ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው በኢትዮጵያ ከተሞችና በኡልሳን ከተማ መካከል ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የደቡብ ኮሪያውን ሃዩንዳይ የመኪና ኩባንያ እንደ ምሳሌ በመጥቀስ ሀገሪቱ የአፍሪካን ገበያ ለመድረስ ኢትዮጵያን እንደ ስትራቴጂክ መዳረሻ እንደምትጠቀም ጠቁመዋል።
በዚህም የከተማዋ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ በአፍሪካ የንግድ ገበያ ሰፊ እድል እንዲኖራቸው ይሰራል ብለዋል።
አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በከተማዋ በነበራቸው የስራ ጉብኝት የሀዩንዳይ ሞተርስ ኩባንያን መጎብኘታቸውን በደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።