በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ ነው- ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት እየተደረገ ነው- ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ለጨረታ የሚቀርቡ የኢትዮጵያን ቅርሶችን ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ገለፀ።
የብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል ዶክተር አሉላ ፓንክረስት ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተለያዩ ዘመናት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው በአውሮፓ የሚገኙ ቅርሶች በቁጥር በርካታ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ውድ ቅርሶች ወደ ሀገር እንዲመለሱ የበኩሉን ጥረት ማድረጉን አስታውሰዋል።
በመቅደላው ጦርነት በእንግሊዝ ጦር ተዘርፈው ከተወሰዱ ቅርሶች መካከል ከ20 በላይ መመለሳቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከተዘረፉ ቅርሶች መካከል የተመለሱ እንዳሉ ጠቁመው፤ ከግለሰቦች ከተመለሱት መካከልም በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የተቀመጡ እንዳሉ ገልፀዋል።
ይህም ሆኖ ከመቅደላ ከተዘረፉ ቅርሶች መካከል ብራናዎች፣ ንዋየ-ቅድሳት እና የነገሥታት የወግ ዕቃዎች መመለሳቸውን ገልፀው፤ አሁንም በውጭ ካሉ ቅርሶች ብዛት አኳያ ሰፊ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በእንግሊዝ አገር ብቻ በ27 ሙዚየሞች ውስጥ የኢትዮጵያ ቅርሶች ይገኛሉ ያሉት ዶክተር አሉላ፤ ቅርሶቹን የማስመለስ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በተለይም በግለሰቦች እጅ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ለጨረታ እየቀረቡ በመሆኑ፤ ከጨረታ በመከላከል ወደ ሀገር እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው ያነሱት።