ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሐጅና ዑምራ ተጓዦች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለሐጅና ዑምራ ተጓዦች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  መስፍን ጣሰው ገለፁ። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ የሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር የኢፍጣር መርኃ-ግብር ትናንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል።


 

በመርኃ-ግብሩ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ፤ እንኳን ለታላቁ የረመዳን ወር አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ "በዚህ ታላቅ የመሰባሰቢያና የአብሮነት ወር ኢፍጣር ከኛ ጋር ለማሳለፍ እዚህ በመገኘታችሁ የላቀ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ" ብለዋል።

አየር መንገዱ የደንበኞቹን ምቾት ለመጠበቅ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በየዓመቱ እያሻሻለና እያሰፋ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን የሐጅና ዑምራ ጉዞዎች ለዓመታት ለደንበኞቹ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰዋል።

እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዘንድሮም ከመላው አፍሪካ የሐጅና ዑምራ ጉዞ ማድረግ የሚፈልጉ ምዕመናንን ለማገልገል አየር መንገዱ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ለሐጅና ዑምራ ተጓዦች የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ አየር መንገዱ ላደረገው የኢፍጣር መርኃ-ግብር ምስጋና አቅርበዋል።


 

ምክር ቤቱ ከአየር መንገዱ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም