በአፍሪካ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል

320

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 16/2016(ኢዜአ)፦ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል።

የአፍሪካ ጨዋታዎች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና አክራ መካሄዱ ይታወቃል።

በውድድሩ ከ53 ሀገራት የተወጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።


 

ኢትዮጵያም በአምስት የኦሊምፒክ ውድድሮችና አራት ኦሊምፒክ ያልሆኑ ስፖርቶች በድምሩ በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች መሳተፏ ይታወቃል።

በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ የጠረጴዛና ሜዳ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ በ9 የወርቅ፣ 8 የብር፣ 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ኢትዮጵያ ካገኘቻቸው 22 ሜዳሊያዎች 18ቱ የተገኙት በአትሌቲክስ ነው፤ 7 የወርቅ 7 የብርና 4 የነሐስ ሜዳሊያ በአትሌቲክሱ ተገኝቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቦክስ ሁለት የወርቅና አንድ የነሐስ እንዲሁም በብስክሌት አንድ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በውድድሩ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድንም ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ የሚገባ መሆኑን ኢዜአ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ልዑካን ቡድኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ያደርጉለታል ተብሎ ይጠበቃል።

በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ 101 ወርቅ 46 ብር 42 ነሐስ በድምሩ 189 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን በበላይነት አጠናቃለች።

ናይጄሪያ በ47 ወርቅ፣ 33 የብር እና 40 የነሐስ በድምሩ 120 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በ32 ወርቅ 32 የብር እና 42 የነሐስ በድምሩ 106 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በውድድሩ ከተሳተፉ 53 ሀገራት 45ቱ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ የገቡ ሲሆን አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና እና ሞሮኮ ከአራተኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም