በህብር የተገነባ ገድል

2418

 

"የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንጨርሰዋለን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የምንጨርሰው ልጆቻችንን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስም እንደምንችል እንዲያውቁት ስለምንፈልግም ጭምር ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የትውልድ አሻራ ደምቆ የተፃፈበት የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ።  ይህ ቀን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የረባ ጥቅም ሳይሰጥ ወደ ጎረቤት አገራት ሲፈስ የኖረውን የአባይ ወንዝ ወደ ብርሃን ለመቀየር በቁርጠኝነት በመነሳት የማይቻልን ነገር በይቻላል ወኔ በመቀየር ለዓለም ያሳዩበት፤ ዓለም የተደመመበት ቀን ነው። 

የግድቡ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት በርካታ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት ታሳካው ይሆን? የሚል ጥርጣሬ አዘል ርእስ የያዘ ተከታታይ ዘገባ አስነብበዋል። ኢንተርናሽናል ሪቨርስ የተሰኘው ድረ ገጽ በፈረንጆቹ 2011 ‘Can Ethiopia Afford the Grand Renaissance Dam?’ በሚል ርእስ ባወጣው ሰፋ ያለ ዘገባ ግድቡን ለመገንባት ከሚያስፈልገው ጠቅላላ ገንዘብ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሊያዋጡ የሚችሉት በጣም ጥቂቱን ብቻ በመሆኑ ግንባታው ሊሳካ አይችልም በሚል ትንበያውን አስቀምጦ ነበር።  

የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው ግሪን ፕሮፊት የተሰኘ ድረ ገጽ የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ ‘Defiant Ethiopia is proceeding with its plan to build the Grand Millennium Dam on the Nile River, but what kind of dam can they build without cash flow? ..... there’s one important problem: Ethiopia lacks the necessary funds to see the project to completion. In fact, they can barely get it off the ground.’ በማለት ኢትዮጵያ ግድብ መገንባት የሚያስችል ገንዘብ ስለሌላት ፕሮጀክቱ ሊተገበር አይችልም ሲል ደምድሟል፤ ተሳልቋልም።  

በወቅቱ የዚህ ዓይነት ግምት የብዙዎቹ ተንታኞች መንደርደሪያ ነበር። “ኢትዮጵያ ደሃ አገር ስለሆነች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር ካልተገኘ በስተቀር ፕሮጀክቱ ወደ ፍፃሜ መድረስ አይችልም” የሚል ድምዳሜ ለመስጠት ተንታኞቹ ብዙም አይቸገሩም ነበር።  ‘ግድቡ የጥራት ችግር ስላለበት ይደረመሳል’ ከሚለው ዘመቻ ጀምሮ በግድቡ ላይ ጥቃት እንደሚፈጸምበት ተደጋጋሚ የዛቻና የማስፈራሪያ መልእክቶች ተስተጋብተዋል።      

በጥቅምት ወር 2013 ዓ. ም የቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ግብጽ ተጎጂ እንደሆነች አቋም በመያዝ "ግብፅ በዚህ መንገድ መቀጠል ስለማትችል ሁኔታው አደገኛ ነው፤ ግብፅ የህዳሴ ግድብን ታፈነዳለች፤ አሁንም በግልፅ እናገረዋለሁ ግብፅ በድጋሚ ታፈነዳዋለች" የሚል ጠንከር ያለ የዛቻ መልእክት አስተላልፈዋል። 

ኢትዮጵያውያን ውኃ ወደ ናይል እንዳይፈስ የሚያቆም ግድብ ገንብተዋል ሲሉ የገለጹት ትራምፕ ግብጽ ትንሽ በመበሳጨቷ ልትወቅሷት አትችሉም ሲሉም አክለዋል። "ግብፅ የህዳሴ ግድብ እንዲገነባ መፍቀድ አልነበረባትም፤ የስምምነት ሀሳብ ለአገራቱ ባቀርብም ኢትዮጵያ ስምምነቱን ሳትቀበል ቀርታለች። እንደዚያ ማድረግ አልነበረባቸውም ይህ ትልቅ ስህተት ነው። በዚህም ምክንያት የምንሰጣቸውን ብድር አቁመናል። ስምምነቱን ካልተቀበለች በስተቀር ኢትዮጵያ ገንዘብ አታገኝም " ብለዋል።

አትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመገንባትና ዳር ለማድረስ ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ የተለያዩ ኃይሎች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል። በዚህም ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበር አገር ወይም ተቋም ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለሆነም የነበረው አማራጭ አንድም ግድቡን አለመሥራት፣ አለበለዚያ ወጪውን በራስ አቅም መሸፈን ነበር፡፡ ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ ወጪውን በራሱ አቅም በመሸፈን መስዋዕትነትን ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን በተግባር አረጋገጠ። 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር ኢትዮጵያውያን ገጠር ከተማ ሳይሉ፤ በአገር ውስጥና በውጭ ከጫፍ እስከ ጫፍ በእልህና በቁጭት በመነሳሳት ግድቡን በራሳቸው አቅም ገንብተው ዳር ለማድረስ ቃል ኪዳን ያደረጉት። ለግንባታው የሚውል ድጋፍ በገንዘብና በዓይነት በተለይም የቦንድ ሽያጭ፣ በ8100 አጭር መልእክት እና በእጣ አገልግሎት ህዝቡ ተረባረበ፤ የማይቻለውን እንደሚቻል ለዓለም አሳየ።   

በበርካታ ፈተናዎችና ጫናዎችን ሳይበገር ግንባታው የቀጠለው የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት የሲቪል ስራው 99 በመቶ መድረሱንና የኤሌክትሮ ሜካኒካል በተለይም የተርባይንና ጄኔሬተር ተከላ ሥራው 78 በመቶ መጠናቀቁን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባት ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በቅርብ ያወጣቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።  

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል የህዳሴው ግድብ ቀዳሚው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ "የታላቁ ህዳሴ ግድብን እንጨርሰዋለን፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የምንጨርሰው ልጆቻችንን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስም እንደምንችል እንዲያውቁት ስለምንፈልግም ጭምር ነው" በማለት አረጋግጠዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጋር የተያያዙ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ቢኖሩባትም የግድቡን ሥራ ለአፍታም አላቋረጠችም።

በአሁኑ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈፃፀም ከ95 በመቶ በላይ መድረሱን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል። ዘንድሮ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት ይከበራል፤ መሪ ሀሳቡም "በኅብረት ችለናል!" የሚል ሲሆን ኢትዮጰያውያን ችለው ያሳዩበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። 

እዚህ ድል ላይ የተደረሰው በመንግሥት ቁርጠኛ አቋምና የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ነው። ባለፉት 13 ዓመታት ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ተሳትፎ ተጀምሮ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ ወራቶች የቀሩት ይህ ታላቅ አገራዊ ፕሮጀክት የአገሪቱን የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ከማሻሻሉም ባሻገር ለጎረቤት አገራት ተደራሽ በማድረግ ቀጣናውን በማስተሳሰር በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም