በብልፅግና ፓርቲ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቃል በተግባር የተረጋገጠባቸው ናቸው -የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በብልፅግና ፓርቲ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቃል በተግባር የተረጋገጠባቸው ናቸው -የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016(ኢዜአ)፦ በብልፅግና ፓርቲ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቃል በተግባር የተረጋገጠባቸው የስኬታማነት ማሳያዎች መሆናቸውን የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ አባላት የማጠቃለያ የውይይት መድረክ "ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተካሄዷል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ፤ ፓርቲው በጥቂት አመታት ውስጥ ሰፋፊና ስኬታማ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተከናወኑ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያ የላቀ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል።
በዚህም ከአፍሪካ ከአንድ እስከ አምስት ከፍተኛ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ ችላለች ነው ያሉት።
አዲስ አበባን ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ግዙፍ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ቃል በተግባር የተረጋገጠባቸው የስኬታማነት ማሳያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባን የብሔራዊ ትርክት ማሳያ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም በተለያዩ መድረኮች ከህብረተሰቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የፓርቲው አባላት የውስጥ ፓርቲ ዲሲፕሊን፣ አንድነትን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አዳነች አቤቤ፤ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በአለም መድረኮች ጭምር እውቅና እየተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳደጉ ፕሮጀክቶች በቂ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ሀገሩን እና ህዝቡን የሚመስል፣ ለትውልድ የሚሰራ፣ ሰው ተኮር ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።
ያለፉት አመታት ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም ያሉት ከንቲባዋ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢገጥሙም መሻገር የተቻለው በፖለቲካ ዓላማ ጽናት እና በመርህ በመቆም ነው ብለዋል።
የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶች ለቀጣይ ስራዎች ስንቅ እና መነሳሳት የሚፈጥሩ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ሂደት ተሳትፎ የነበራቸውን ሁሉ አመስግነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው በየደረጃው ሲካሄዱ የነበሩ ውይይቶች ለቀጣይ ተልዕኮ አቅም የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
ውይይቶቹ በከተማ አስተዳደሩ ባሉ 4 ሺህ 97 መሰረታዊ ድርጅቶች በክፍለ ከተሞችና በ136 ወረዳዎች በስኬት መከናወናቸውን ገልጸዋል።