ቀጥታ፡

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ የማሻሻያና የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016(ኢዜአ)፦የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠትና መቋቋም የሚያስችሉ የማሻሻያና የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ተቋም በማቋቋም በደኖች ላይ ሊደርሱ ለሚችሉ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የሥራ አመራር አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌቱ ንጉሴ፤ ከ56 ዓመታት በላይ የተሻገረው ተቋሙ ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል ብለዋል።

አሁን ላይ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ስርዓትን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተቋማዊ የማሻሻያና የለውጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ መነሻነትም የአሰራር ሥርዓት የሚመራበት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር የፖሊሲ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ በ27ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ መጽደቁን አስታውሰዋል።

በፖሊሲው በአገር አቀፍ ደረጃ በአደጋ ስራ አመራር ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በራስ አቅም ምላሽ መስጠት እንደሚቻል አንስተዋል።

አደጋን መከላከል፣ መቆጣጠር፣ የከፋ ጉዳት እንዳይደረስ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የተናበበ መዋቅር መዘርጋት፣ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲክስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የህዝብ ቁጥር ዕድገትና የተቋማት ትብብርን ማሳደግ የፓሊሲ ክለሳው መነሻ ሃሳቦች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ከቀበሌ እስከ ፌደራል ተዋረዳዊ የአደጋ ወሰን ብይን በማስቀመጥ በምላሽ አሰጣጥ ሂደት ወቅት ሁሉም መዋቅር የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የሚያደርግ ስለመሆኑም አስንተዋል።

ቅድመ አደጋ ቅነሳ፣ ምላሽ መስጠት፣ አቅም መፍጠር፣ በሰብዓዊ አቅርቦት ማድረግና መልሶ ማቋቋም፣ ድህረ አደጋ ልማትና በቂ ሃብት ማሰባሰብ ዋነኛ የፖሊሲው ዓላማዎች እንደሆኑም አስረድተዋል።

በፖሊሲው የተመላከቱ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት መምራት የሚችል የሰው ሃይል በማዋቀር በጥናት ላይ የተመሰረተ አዲስ ተቋማዊ የማሻሻያ አደረጃጀት መዘርጋት እንደተቻለ ገልጸዋል።

በክልል ደረጃ የሚገኙ የአደረጃጀት ትስስሮችን በማጠናከር ሁሉም መዋቅርና የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንደሚደረግም አንስተዋል።

በፖሊሲው መነሻነትም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ተጠሪ የሆኑና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ተቋት እንደሚቋቋሙ አስታውቀዋል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት በማቋቋም በተለይም በደኖች ላይ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘውን የእሳት አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በደኖቿ ላይ የሚከሰት የእሳት አደጋን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሂሊኮፕተር ትዋስ ነበር ያሉት አቶ ጌቱ፤ ይህን ለማስቀረትም የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ተቋም እንዲኖር ይደረጋል ብለዋል።

አገልግሎቱ ሂሊኮፕተሮችና ጀልባዎች እንዲኖሩት በማድረግም የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተቋማዊ አደረጃጀቶችን በማጠናቀቅ ከተባባሪ ተቋማት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችል የስራ ስምምነት በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ሰላምን በማጽናት፣ ልማትን በማፋጠንና አደጋን ምላሽ በመስጠት በ2030 "ለአደጋ የማይበገር ማህበረሰብ መፍጠር" የሚል ራዕይ አንግቦ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም