የልማትና መልሶ ግንባታ ስራው ለከተማዋ ውበት ለእኛም አዲስ የህይወት ምእራፍ የከፈተ ነው- የፒያሳ አካባቢ የልማት ተነሽዎች - ኢዜአ አማርኛ
የልማትና መልሶ ግንባታ ስራው ለከተማዋ ውበት ለእኛም አዲስ የህይወት ምእራፍ የከፈተ ነው- የፒያሳ አካባቢ የልማት ተነሽዎች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የልማትና መልሶ ግንባታ ስራው ለከተማዋ ውበት ለእኛም አዲስ የህይወት ምእራፍ የከፈተ ነው ሲሉ የፒያሳ አካባቢ የልማት ተነሽዎች ተናገሩ።
የዓለም የዲፕሎማሲ ማእከልና የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባ ደረጃዋን የምትመጥን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ በመንግስት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
የመዲናዋ ነዋሪዎችም ከአስቸጋሪና ብዙ ነገሮች ከተጓደሉበት የአኗኗር ዘይቤ በመውጣት በምቹ ሁኔታ እንዲኖሩ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በማደስ እንዲሁም በአዲስ መልክ በመገንባት በርካቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲኖሩ ተደርጓል።
በአዲስ አበባ በመልሶ ማልማት ላይ ከሚገኙት አካባቢዎች መካከል ፒያሳና አካባቢው ሲሆን ነዋሪዎችም በሌሎች አካባቢዎች መኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው መኖር ጀምረዋል።
ፒያሳ አካባቢ ይኖሩ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወይዘሮ አበበች ዘለቀ፤ ከስድስት ቤተሰቦቻቸው ጋር በጣም አስቸጋሪ ህይወት ይመሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
የነበሩበት ቤት ለቤተሰቡ የማይበቃ ስለነበር ለመኝታ ከመቸገራቸው ባለፈ በዝናብ ወቅትም ኖሯችን ፈታኝ ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
በዚሁ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው እና ወይዘሮ አስቴር ደምስ፤ ከቤቱ ጥበትና አስቸጋሪነት የተነሳ ቀን ከቤተሰብ ጋር ሰብሰብ ለማለትና በማታም መኝታ ዘርግቶ ለማረፍ ጭንቅ ነበር ይላሉ።
በአካባቢው የብዙዎቻችን ህይወት በእጅጉ አስቸጋሪ፣ ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ ለጤናም ጠንቅ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ።
በመሆኑም የልማትና መልሶ ግንባታ ስራው ለከተማዋ ውበት ለእኛም አዲስ የህይወት ምእራፍ የከፈተ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የነበርንበት ህይወት ባኗኗርም ይሁን በጤና በርካታ አስቸጋሪ ህይወት አሳልፈናል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን ላይ አዲስ ህይወት መምራት ጀምረናል፤ በዚህም ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።