የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከልና ምርታማነትን ለመጨመር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከልና ምርታማነትን ለመጨመር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ግብርና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016(ኢዜአ)፦ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ማነቆ የሆነውን የአፈር አሲዳማነት ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የኢትዮጵያ የአፈር ሀብት መረጃ ፕሮጀክት እኤአ በ2018 ያጠናው ጥናት እንደሚያመላክተው በኢትዮጵያ ሊታረስ ከሚችለው መሬት ሰባት ሚሊዮን ሄክታሩ ወይም 43 በመቶ የሚጠጋው አሲዳማ ነው።
ከዚህም ውስጥ ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ወይም 28 በመቶ በጠንካራ አሲዳማነት ተጠቅቷል።
በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሊሬ አብዮ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ የአፈር አሲዳማነት የሚያጠቃቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ አካባቢዎችን መሆኑን ገልጸዋል።
ለግብርና ስራ ትልቁ ግብዓት በሆነው አፈር ላይ የሚያጋጥመው አሲዳማነትና ጨዋማነት በምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑንም አቶ ሊሬ አስረድተዋል።
ጉዳቱ ቦታ ሳይሰጠው ቢቆይም በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት ለችግሩ መፍትሄ የሚሆኑ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት 200ሺህ ሄክታር አሲዳማ መሬትን በኖራ ለማከም የግብርና ሚኒስቴር ኖራ አቅርቦት ስርዓቱን ማሻሻልና ተደራሽነቱን ማስፋት ላይ ከክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና አሲዳማነትን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ሊሬ አንስተዋል።
አሲዳማ አፈርን መቋቋም የሚችሉ የሰብል አይነቶችን በመዝራት በምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በጠንካራ አሲዳማነት ከተጠቃው ሶስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር አፈር እስካሁን 135 ሺህ ሄክታሩን በኖራ ማከም መቻሉን ገልጸው፤ ከችግሩ ስፋት አኳያ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የአፈር ለምነትና ጤንነትን ለመጠበቅና አሲዳማነትን ለመከላከል እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር መሆኑንም አቶ ሊሬ ተናግረዋል።
መርኃ-ግብሩ አለምአቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ከመከላከል ባለፈ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለው በመግለጽ።
በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከልና ለመቀነስ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአፈር መከላትን በመከላከል አፈር ውስጥ ያሉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የመጠበቅ ስራ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከውጭ ከምታስገባው ማዳበሪያ ውስጥ 28 በመቶ ያህሉ በጠንካራ አሲዳማነት ለተጠቁ ማሳዎች እንዲውል ታሳቢ የሚደረግ ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የአፈር አሲዲማነት የሚፈጠረው በአፈር ውስጥ ያለው የፒ.ኤች (ኮምጣጣነት) መጠኑ ከ 7 በታች ሲሆንና የሀይድሮጅን፣ አለሙኒየም፣ አይረንና ማንጋኔዜ የተባሉት ንጥረ-ነገሮች ክምችት ሲበዛ ሲሆን የካልሲየም፣ ማግኔዥየም፣ ፖታቪዬምና የመሳሰሉት ንጥረ-ነገሮች መጠን ደግሞ ሲያንስ ነው።